በአሽባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ቅድመዝግጅት መጠናቀቁን የአደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

325

ባሕርዳር፡ ታሕሳስ 2/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን በአሽባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተፈናቀሉ ዜጎችን አስመልክቶ መግለጫ ሠጥቷል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም አሽባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልል ባደረገው ወረራ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ወገኖች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በአጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ከ7 ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ ጠላት ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ነው የገለጹት፡፡
ኮሚሽነር ዘላለም አሽባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ባደረሰው ጉዳት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቀያቸው ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ሥራው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነር ዘላለም ማኅበረሰቡ፣ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ዲያስፖራዎች በተጠናከረ መንገድ ተፈናቃዮችን ሲረዱ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ስንቅን፣ አልባሳት እና የምግብ ማብሰያ ቁሳቁስ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ችግሩን መንግሥት ብቻውን መወጣት እንደማይችል እና በርካታ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉ ኮሚሽነር ዘላለም አስገንዝበዋል፡፡

ነፃ በወጡ አካባቢዎች ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ማኅበረሰቡ መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዲያስፖራዎች እና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ርብርብ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡

በችግር ውሥጥ ያሉ ወገኖች እስኪቋቋሙ ድረስም ማኅበረሰቡ፣ መንግሥት እና በሀገር በውስጥ በውጭም ያሉ ዲያስፖራዎች ካሁን በፊት ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮሚሽነሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በርካታ ሥራዎች እና ድጋፎች ያስፈልጋሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ሂደት ውስጥ ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አሠራርን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ድጋፉ በመንግሥት አሠራር ውስጥ በአንድ ቋት የሚሰበሰብ መሆኑን ተገንዝቦ በዚህ አግባብ ብቻ መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በጦርነቱ በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም ችግሩን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡ፣ መንግሥት ዲያስፖራዎች እና ረጅ ድርጅቶች ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማውደሙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወገኖች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሕይወታቸውን ይገፉ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ወገኖች ለመርዳት የተንቀሳቀሰ አንድም ዓለማቀፍ የሠብዓዊ ድጋፍ አድራጊ ተቋም አለመኖሩንም አስረድተዋል፡፡ በጠላት ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች በምግብ እና በመድኃኒት ችግር የሰው ሕይወት ማለፉንም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq በዌብሳይት amharaweb.com በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleዓለም ዓቀፍ ገለልተኛ እና ለእውነት ቆመናል የሚሉ ተቋማት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለዓለም እንዲያጋልጡ ጥሪ ቀረበ፡፡
Next articleበጎንደር ከተማ አስተዳደር የሲቪክ ማኅበራት ለዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ አደረጉ፡፡