
ሕዳር 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግኖች በግንባር አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ሲፋለሙ ሕዝቡ በስንቅ እና የተጎዱትን በመንከባከብ የቆየ ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን አሳይቷል፤ እያሳየም ይገኛል። በዋግ ግንባር የአንድ ሰፈር ሰዎች የሰብዓዊነት ጀብድ ፈጽመዋል።
ባለታሪኩ ወጣት ቀለቡ እንግዳው ይባላል። በምዕራብ በለሳ ነዋሪ ነው። የሦስት ልጆች አባትም ነው። ወራሪው ቡድን አማራን ሲገድል፣ ንብረቱን ሲዘርፍና ሲያወድም እያየ ችሎ ዝም ማለት አቃተው። ሀገር ተደፍራ መንግሥት የክተት ጥሪ ሲያስተላልፍ አቅመ ደካማ ወላጆቹን፣ ወንድምና እህቶቹን፣ ልጆቹን እና ባለቤቱን ትቶ የግል መሳሪያውን ይዞ ሕዳር 14/2014 ዓ.ም በዋግ ግንባር “እርግቢት አንባ” ከተባለው ቦታ ከወገን ጦር ጋር በመቀናጀት ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጋር ፍልሚያ ጀመረ።

በነበረው ከፍተኛ ውጊያ አብረውት ከተሰለፉት ጓዶቹ ጋር ጠላትን እየለበለቡ ሳይታሰብ ጠላት ቀጣና ውስጥ ጥሰው ይገባሉ። ወጣቶቹ በጠላት ላይ ባደረሱት ከፍተኛ ኪሳራ በጠላት ጥርስ ውስጥ ገቡ። ጠላት ከቻለ ለመያዝ ካልቻለ ደግሞ ለመደምሰስ ያለ የሌለ ኀይሉን ተጠቅሞ በቆረጣ ገብቶ ጥቃት ሰነዘረ። ጀግኖቹም የሞት ሽረት ውጊያ በማድረግ ጠላትን እንደ እግር እሳት መለብለቡን ቀጠሉ። ይኹን እንጅ ጠላት ኃይሉን ጨምሮ ሲመጣ እነ ቀለቡ ለማፈግፈግ ወሰኑ። ወደ ኋላ በማፈግፈግ ላይ እንዳሉም አንዱ ጓዳቸው ተሰዋ፤ ወጣት ቀለቡ ተመትቶ ቆሰለ፤ የአቶ ቀለቡ የአክስት ልጅ ግን ጠላትን እየረፈረፈ ወደ ኋላ አፈገፈገ። ጠላት ያመለጠውን ወጣት ተከትሎ የጥይት ዶፍ ማውረዱን ተያያዘው።
የጠላትን አደገኛ አመጣጥ የተመለከተው ወጣት ቀለቡ ከቆሰለበት ቦታ ተንከባሎ በአካባቢው በሚገኝ ቁጥቋጦ ተደበቀ። ጠላትም ወጣቱን ቁስለኛ መፈለግ ጀመረ፤ ሊያገኘው ግን አልቻለም። ጠላት ቀኑን ሙሉ አካባቢውን እየተዘዋወረ አሰሰ። ወጣት ቀለቡም በተደበቀባት የደደኾ ቁጥቋጦ ውስጥ ራሱን ደበቀ። ከፍተኛ ደም ፈሶታል። የለበሰው ልብስ በፈሰሰው ደም ርሷል። በውኃ ጥም መናገር አቅቶታል፤ ተዳክሟል።

ከሁለተኛው ቀን በኋላ ጦርነቱ ጋብ ብሏል። በዚህ ጊዜ አቶ ሞገሴ ማሞ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ አዝመራ ለመጎብኘት በአካባቢው ደረሱ። ወጣት ቀለቡ አቶ ሞገሴን ድንገት ተመለከተ። ወጣቱ እርዳታ እንዲያደርጉለት በደከመ ድምጽ ተጣራ። አቶ ሞገሴም ጠላት ቢደርስባቸው ሊያርፍባቸው የሚችለውን የጭካኔ በትር ማሰላሰል ጀመሩ። ወዲያውኑም አንድ ዘዴ ዘየዱ፤ ወጣቱ ካለበት እንዲያድር እና የጠላት እንቅስቃሴ ታይቶ ወደ መኖሪያ ቤት እንደሚወስዱት ነገሩት። ከቤቱ እስኪወስዱት ግን በተደበቀባት ቦታ አብሮ በማደር እንደተንከባከቡት ወጣት ቀለቡ ነግሮናል።
ስለ ሁኔታው ያነጋገርናቸው አቶ ሞገሴም ይህንኑ ነው ያጠናከሩልን። “ጦርነቱ በተካሄደበት አካባቢ ማሳየን ለማየት ሳልፍ አንድ በጥይት ተመትቶ የቆሰለ ሰው እርዳታ ፈልጎ በለኾሳስ ተጣራ። ወደ ወጣቱ ተጠግቼ ሳናግረው የወገን ጦር መኾኑን ነገረኝ። ብዙ ደም በመፍሰሱ ተዳክሟል። አካባቢው በጠላት ቁጥጥር ስር ስለነበር ወዲያውኑ ወደ ቤት ለመውሰድ ስጋት አደረብኝ። ይልቁንም ባለበት ኾኖ አብሮ በማደር መንከባከቡን እንደ አማራጭ ወሰድኩ” ሲሉ የነበረውን ኹኔታ ነግረውናል።
አቶ ሞገሴ በሦስተኛው ቀን በጀግንነት ሲፋለም የተጎዳውን ቀለቡን ወደ ቤት ለመውሰድ ዘዴ ዘየዱ፤ የተጎዳውን ታጋይ ህይወቱ ያለፈ አስከሬን በማስመሰል ወደ ቤት መውሰድ፤ ጠላት እውነታውን ከደረሰበት ደግሞ የሚመጣውን መቀበል ነበር። በሦስተኛው ቀንም አቶ ሞገሴ የተጎዳውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመኾን በጫካ አቆራርጠው ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመውሰድ ለ12 ቀን ለነጻነት በአይበገሬነት ለተፋለመው ጀግና በቤታቸው እርዳታ አደረጉለት።
በ12ኛው ቀን የተጎዳውን ታጋይ ለመንግሥት በማስረከብ ሕክምና እንዲደርስ አደረጉ። ባለቤታቸው ወይዘሮ ብርሃኔ ወርቁ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ያሳዩት ሰብዓዊነት ከፍተኛ ነበር።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ