
የወገን ጦር አባል ምሬ ወዳጁ ጠላት መውጫ መግቢያ እያጣ ነው ብለዋል። በጥምረት እየተደረገ ባለው ውጊያ ጠላትን እያሳደዱትና በየደረሰበት እየደመሰሱት መሆኑን ነው የገለፁት። በወገን ጦር ያለው ጥምረት የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል። ጠላት የቻለውን ያክል ቢታገልም የወገን ጦር ከባድ ምት መቋቋም ተስኖታል ነው ያሉት፡፡
ማንም ጠላት በኢትዮጵያ ላይ እነሳለሁ ቢል መጨረሻው #መጥፋት መሆኑንም ገልጸዋል። ትጥቃቸውና ስንቃቸው፣ ማንነታቸውና ጉልበታቸው ሁሉ ሕዝብ እንደሆነ ያነሱት የወገን ጦር አባሉ ሕዝብ እስካሁን እንደኮራብን ወደ ፊትም የበለጠ ይኮራብናል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሐፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ በምዕራብ ወሎ ግንባር በወራሪውና አሸባሪው ቡድን ተወረው የነበሩ ሥፍራዎች ነፃ እየወጡ ነው ብለዋል። ጠላት መውጫ ለማግኘት ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሟል ያሉት ኮሌኔል ባምላኩ የወገን ጦር የቀደመ የአባቶቹን ታሪክ በመድገም ጠላትን #እየቀበረው ነው ብለዋል።
ጠላት ያለ የሌለ ኃይሉን ቢጠቀምም የጀግናውን የወገን ጦር ከባድ ምት መቋቋም እንዳልቻለም ተናግረዋል።
የወገን ጦር ተናቦ በመሥራት አኩሪ ተግባር እየፈፀመ ነውም ብለዋል። ከሕዝብና ከፖለቲካ መሪዎች ጋር በመናበብ አስደናቂ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። ጠላት ተፍረክርኮ የመዋጋት አቅሙን እንዳጣም ተናግረዋል።
ጠላት የወገንን ሠራዊት ከፍተኛ የሆነ የውጊያ ብቃት ስለተረዳ ኃይል ቢጨምርም ሙትና ቁስለኛ እየሆነ መቅረቱን አስታውቀዋል። ጠላት ፈርሶ መዋጋት የማይችልበት ደረጃ መድረሱንና ቁስለኛውን እየተወ እየፈረጠጠ መሆኑንም ገልጸዋል። የወገን ጦር ጠላትን እግር በእግር እየተከታተለ የያዘውን እያስጣለው፣ ለመውጣት ያሰበውንም አይቀጡ ቅጣት እየቀጣው መሆኑን ነው የተናገሩት።
የወገን ጦር ከድል ላይ ድል እንዲጨምር ሕዝቡ ያለውን እያቀረበ፣ አብሮ እየተዋጋ፣ መረጃ እየሠጠ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ሕዝቡ ለወገን ጦር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ጠላት እጅ እንዲሰጥ ካለበለዚያ በገባበት እንዲቀር የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። ጠላት ምንም አይነት ነገር ይዞ እንዳይወጣና እርሱም እንዳይወጣ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation