
ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2012 ዓ/ም (አብመድ) በጎንደርና አካባቢዉ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ዙሪያ አንዳንድ ሚዲያዎች ሲዘግቡት የነበረዉ የተሳሳተ መረጃ ሕዝብን እያደናገረ እንደሆነ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡
በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት ሀገርነ ለማፍረስ እንጅ ለመገንባት እየዋለ አለመሆኑን በደባርቅ ከተማ አስተዳደር አስተያዬታቸዉን ለአብመድ የሰጡ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡
ነዋሪዎቹ እንዳሉት በጎንደርና አካባቢዉ በተከሰተዉ ግጭት ዙሪያ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃች የዘገቡበት መንገድ ከሚዲያ የማይጠበቅና ሚዲያዎቹ አማራ ጠል ለመሆናቸዉ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡
‹‹የመገናኛ ብዙኃኑን የክልል መንግሥታት መቆጣጠር ካልቻሉ የኢትዮጵያ ብሮድስካት ባለስልጣን ለምን እርምጃ አይወስድም? ባለስልጣኑ ካላስተካከላቸው የፌደራል መንግሥቱም ጣልቃ በመግባት ይህን ተግባር ሲያራግቡ የነበሩ ሚዲያዎችን ተጠያቂ ሊያደርግ ይገባል›› ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ለሚገኙት ሕዝቦች የሌሎቹ ክልሎች የመገናኛ ብዙኃን ጠበቃ መስለው እንደታዩና ይህም የሚዲያዎቹ እጅ እንዳለበት አመላካች መሆኑን አስተያዬት ሰጭዎቹ ተናግረዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃኑን የብሮድካስት ባለስልጣን ተጠያቂ እንዲያደርም ጠይቀዋል፡፡
በአማራ ክልል የሚገኝ ማንኛውም የወጣት ሲቪክ ማኅበር፣ የማኅበራዊ ሜዲያ አንቂና ሌሎችም ከመሠል አሳሳች የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች አጀንዳ ራሱን እንዲጠብቅም አሳስበዋል፡፡
‹‹በማኅበራዊ ሚዲያዉ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን ተቀብሎ አጀንዳ ማድረግ ሊቆም ይገባል›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ -ከደባርቅ