“ኢትዮጵያ የከበቧትን ጠላቶቿን እያሸነፈች ያለችው ኢትዮጵያዊነት በተባለው ከኢትዮጵያ ብቻ ሊመነጭ በሚችለው ልዩ ኃይል ነው” ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

283
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‘ማነስ አልለመደብንም‘ በሚል ርእስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ “ኢትዮጵያ የከበቧትን ጠላቶቿን እያሸነፈች ያለችው ኢትዮጵያዊነት በተባለው ከኢትዮጵያ ብቻ ሊመነጭ በሚችለው ልዩ ኃይል ነው” ብለዋል።
ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያጋሩት ጽሑፍ ቀጥሎ ቀርቧል።
እባክህ ላክልኝ ፈተና
ዐቅሜን ይነግረኛልና፤
ይላል በዕውቀቱ ስዩም፡፡
ኢትዮጵያን ኈልቈ መሳፍርት ችግሮች ከብበዋታል፡፡ የውስጥ ባንዳው፣ የእናት ጡት ነካሹ፣ ምናገባኝ ባዩ፣ ከችግሯ ሊያተርፍ የሚጥረው፤ ከኢትዮጵያ መፍረስ ሊያተርፍ የቋመጠው ጎረቤት፣ አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጦ ሊያንበረክካት የሚፍጨረጨረው ኃያል ነኝ ባይ፣ ምኑ ቅጡ፡፡ ቀን ቀጥረው ቂም ቋጥረው ነው የተነሡት፡፡ ‹አገቱኒ ከለባት ብዙኃን› የሚለው የደረሰ ነው የሚመስለው፡፡
ግን ድንቅ ሀገር ናት መቼም፡፡ ዳዊት ‹በእኔና በሞት መካከል አንድ ርምጃ ብቻ ቀርቷል› እንዳለው በኢትዮጵያና በሞት መካከል አንድ ርምጃ የቀረ መስሎ ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ መፍረስ ሲያወሩ አፋቸውን እንኳን ያዝ አያደርጋቸውም ነበር፡፡ አዲስ አበባ ያሉ ኤምባሲዎች አዲስ አበባ ተከብባለች ሲሉ ከባቢዎቹን እንደ አሞራ ሲዞሯት ያዩ ይመስሉ ነበር፡፡ በየሰዓቱ ኢትዮጵያን ለቃችሁ ውጡ እያሉ ሲጮሁ ካርታ ዘርግተን ሌላ ኢትዮጵያ ትኖር ይሆን? እያልን እንፈልግ ነበር፡፡ አንዳንዶች ባለ ሀብቶች ሻንጣ ሸክፈው አሜሪካና ዱባይ በንግድና በዕረፍት ስም ላጥ ሲሉ ደግመን የምንተያይ አይመስልም ነበር፡፡
ጠብቄሽ ነበረ በአጥር ተንጠልጥዬ
ከዛሬ ከነገ ትመጫለሽ ብዬ፤
የሚለው ሙዚቃ ከፍተው የሚያዳምጡ ነበሩ፡፡ እርሱ ግን ለጠላቶቻችን ንክሻ አሳልፎ አልሰጠንም፡፡
ኢትዮጵያ ዐቅሟ ያልተነካ ብቻ ሳትሆን ዐቅሟ ያልታወቀ ሀገር ናት፡፡ በተሟላ መልኩ ምን እንዳላት የሚያውቀው ፈጣሪዋ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ያ ሁሉ ዘማች ከየት መጣ? ያ ሁሉ ባለ ሀብት ከየት መጣ? ያ ሁሉ የኪነ ጥበብ ሰው ከየት መጣ? ሚልዮኖች ሆነው ስንቅ የሚያዘጋጁት ከየት ተገኙ? ያ ሁሉ ምድርን ቁና የሚያደርግ ዳያስፖራ የት ነበር? እነዚያ ሁሉ በፈረንጅ አደባባይ የሚሞግቱልን የውጭ ወዳጆች ከየት ተገኙ? ያ ሁሉ በግና ፍየል፣ ያ ሁሉ ላምና በሬ፣ ያ ሁሉ እህልና ፍራፍሬ ከየት ተገኘ? ሚልዮኖችን ከመቀነታቸው ፈትተው የሚያዋጡ የቁርጥ ቀን ልጆች ከየት ብቅ አሉ?
ኢትዮጵያ ለካ ባዕለ ጸጋ ሀገር ናት፡፡ ትልቁ ፈተናዋ ሀብቷን አለመሰብሰቧ ነው፡፡ አንድ ወንዝ ውኃው ስለፈሰሰ ብቻ ተርባይን መትቶ ኃይል አያመነጭም፡፡ ውኃው ተሰብስቦ፣ በቱቦ ውስጥ አልፎ ተርባይኑን መምታት አለበት፡፡ የኢትዮጵያም ዐቅም ተሰብስቦ ወደ አንድ ቋት ከመጣ የማይሰብረው ዐለት፣ የማይሻገረው ገደል የለም፡፡ ጠላቶቻችንም የበለጡን በአንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ተበትነን ስንጠብቃቸው ተሰባስበው መምጣታቸው፡፡
የመሰባሰባችን ኃይል እንዴት ተርባይኑን እንዳነቃነቀው በዓይናችን አይተናል፡፡ የፀሐይ ጨረር በሌንስ አማካኝነት ሲሰበሰብ ኃይል ሆኖ እሳት እስከማቀጣጠል ይደርሳል፡፡ ተበታትኖ የነበረው የኢትዮጵያውያን ዐቅም በኢትዮጵያዊነት ሌንስ ሲሰባሰብ ያቃጠለውን የጠላት መጠን በዓይናችን አይተናል፡፡ በዕውቀቱ ስዩም እንዳለው ፈተናው ዐቅማችንን ነግሮናል፡፡ ሁላችንም የተለያዩ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ሞያዎች፣ ዐቅሞች፣ የመኖሪያ አካባቢዎች፣ የሥልጣን ደረጃዎች፣ የፖለቲካ አመለካከቶችና ፍላጎቶች ሊኖሩን ይችላሉ፡፡ አንድ መሰባሰቢያ ግን ያስፈልገናል፡፡ የኢትዮጵያን ዐቅሞች የምንሰበስብበትና የብልጽግናን ተርባይን የምንመታበት መሰባሰቢያ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት የተሻለ የለንም፡፡
ኢትዮጵያ የከበቧትን ጠላቶቿን እያሸነፈች ያለችው ኢትዮጵያዊነት በተባለው ከኢትዮጵያ ብቻ ሊመነጭ በሚችለው ልዩ ኃይል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ውስጡ ኅብር ነው፡፡ ባለ ብዙ መልክ፣ ባለ ብዙ ጸጋ፣ ባለ ብዙ ባህል ነው፡፡ ሁሉም ግን በኢትዮጵያዊነት ቱቦ ውስጥ ሲያልፍ ተርባይኑን ይመታዋል፡፡ ተርባይኑን ሲመታው ኢትዮጵያዊነት የተባለውን ኒኩሌር ያመነጫል፡፡ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት ሌንስ ሲሰባሰቡ ያልታሰበ ኃይል ያመነጫል፡፡ ሰሞኑን የሆነውም ይሄው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፈተናዎች ተሸንፈው አላለቁም፡፡ ምናልባትም አዳዲስ ፈተናዎች ይገጥሙን ይሆናል፡፡ የአንድ ምእራፍ ማለቅ የሌላ ምእራፍ መጀመሪያ ነው፡፡ ተጀመረ እንጂ አላለቀም፡፡ እንዲህ ባለ ወቅት እንዳንሰባሰብ የሚበትኑን ሁሉ ተርባይኑ እንዳይሠራና የኢትዮጵያ ኃይል እንዳይመነጭ የሚፈልጉ ብቻ ናቸው፡፡ ወይም ትንንሽ ተርባይኖችን የሚያንቀሳቅሱ፣ ለጎጥ ብቻ የሚሆኑ ጅረቶች እንዲፈጠሩ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ትንሽነት ላልለመደች ሀገር ትንሽነት ሊያስለምዱ የሚፈልጉትን – ማነስ አልለመደብንም – እንበላቸው፡፡
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
Previous articleበጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሠራተኞች ገንዘብ በማዋጣት ለወገን ጦር ስንቅ እያዘጋጁ ነው፡፡
Next article“አሸባሪዉን የትግራይ ወራሪ ቡድን “ለማጥፋት በተደረገዉ ዘመቻ የተገኘዉ ድል የኢትዮጵያዉያን የሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ያሳየ ነዉ” የመንግስት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት