“የሽብር ቡድኑ ግፍ በዋግ ሕዝብ ላይ”

164
ሕዳር 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከሰሞኑ በዋግ ግንባር አካባቢዎች በጀግናው የወገን ጦር አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ፈርጥጧል። የሽብር ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ በእነዚህ አካባቢዎች በተደራጀ እና በተቀናጀ መንገድ የመንግሥት እና የግለሰብ ንብረቶችን ዘርፋል፤ አውድሟልም።
የሽብር ቡድኑ ወረራ ሲፈጽም አደረጃጀቶችን ሰርቶ እንደሚሰለፍ በቆዝባ ከተማ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የታዘቡትን ነግረውናል። ነዋሪዎች እንዳሉት የታጠቀው የሽብር ቡድን ቀድሞ ከተሞችን እንደተቆጣጠረ መጋዝኖችን፣ ሱቆችን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤት እና የመንግሥት ተቋማት ንብረቶችን ዘርፏል።
በኾቴሎችም ሕዝባዊ ለመምሰል ከፍለው ሲገለገሉ ከዋሉ በኋላ ማታ አፍነው ቀን የተጠቀሙበትን እና ሆቴሎች ሲሠሩ የዋሉትን ገንዘብ ኹሉ እንደሚዘርፉ ነግረውናል።
መቶ አለቃ እንዳልካቸው ገብረመድን በሽብር ቡድኑ ግፍ ከተፈጸመባቸው ወገኖች መካከል አንዱ ናቸው። መቶ አለቃ እንዳልካቸው በሚኖሩባት ቆዝባ ከተማ የሽብር ቡድኑ በቆየበት አንድ ሳምንት ውስጥ የሕዝብ ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ንብረቶችን ሲዘርፍ፣ የተማሪዎችን መቀመጫ ወንበር በመፍለጥ ለማገዶነት ሲጠቀም ተመልክተዋል።
ከሚተዳደሩባት ሆቴል 200 ጠርሙስ የሚጠጋ ቢራ ከፍለው ከተጠቀሙ በኋላ ሌሊት አፍነው በመውሰድ ባለቤታቸውን አስገድደው 160 ሺህ ብር ወስደዋል። የሽብር ቡድኑ በዚህም አላቆመም፤ ከቤታቸው የነበረውን እህል፣ አልባሳት እና ሌሎች ንብረቶችንም ዘርፏል፤ መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል።
“የአማራ ሰንደቅ ዓላማ ይዘሃል፣ የአማራ ልዩ ኀይልን ትመግባለህ፣ ብልጽግና ጋር ግንኙነት አለህ” በማለት ለሁለት ቀን ያህል በገመድ ታስረዋል። “ይገደል? ወይስ ይለቀቅ?” የሚል ውሳኔ ለማሳለፍ ለገዳይ ኮሚቴ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ይሁን እንጂ ከእሳቸው በፊት በከተማዋ አቶ አማረ ዳኘው በተባሉ ነጋዴ ላይ በፈፀሙት የግፍ ግድያ ምክንያት የተቆጣው ሕዝብ ገንፍሎ በመውጣቱ እና ችግር ፈጥሮባቸው ስለነበር ድጋሚ ለችግር ላለመጋለጥ በሚል እንደለቀቋቸው ነግረውናል።
መቶ አለቃ እንዳልካቸው እንዳሉት የሽብር ቡድኑ አቶ አማረ ዳኘው የተባሉ የከተማዋን ንጹህ ነጋዴ 20 ሺህ የሚጠጋ ብር ከቀሙ በኋላ ወደ ጫካ በመውሰድ በአውቶማቲክ ጥይት ደብድበው በግፍ መግደላቸውን ገልጸውልናል።
መቶ አለቃ እንዳልካቸው የሽብር ቡድኑ ከግለሰብ ኪስ በመግባት አንድ ብር እንኳ ሳይቀር በሰደፍ በመደብደብ ነጥቀዋል ነው ያሉት።
የሽብር ቡድኑ ዓላማው የማኅበረሰቡን ንብረት በማውደም ማጎሳቆል ላይ አልሞ የተነሳ በመኾኑ ለመፋለም መነሳታቸውን ገልጸዋል። ሕዝቡም ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ ክብሩን ሊያስከብር ግንባር ይገባልም ብለዋል። በጠላት ቁጥጥር ስር የሚገኘው ማኅበረሰብም ከጠላት ነጻ ለመውጣት እና የሽብር ቡድኑ የዘረፈውን ሀብት ይዞ እንዳይወጣ በስውር በመደራጀት በደፈጣ ሊፋለም እንደሚገባ መክረዋል።
አቶ በየነ አላምረውም ከ200 ሽህ ብር በላይ ንብረት በሽብር ቡድኑ መዘረፋቸውን ነግረውናል። አቶ በየነ እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ሱቃቸውን ገንጥሎ በመግባት የተከማቸውን ሸቀጥ በሙሉ መዝረፉን ነው የነገሩን። የሽቡር ቡድኑ ከአራት ጊዜ በላይ በመመላለስ ግፍና በደል እንዳደረሰባቸውም ገልጸዋል።
ወጣት ዋግሹም ወርቁም ሌላኛው የሽብር ቡድኑ ሰለባ ነው። የሽብር ቡድኑ በከተማዋ እንደገባ እንዳበደ ውሻ በየ ቤቱ እየዘለለ በመግባት ያገኘውን ኹሉ መዝረፉን ነግሮናል።
በላቡ ያፈራውን የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እና ይለብሳቸው የነበሩትን አልባሳት ሳይቀር በሙሉ መዘረፉን ነው ወጣት ዋግ ሹም የነገረን።
የቆዝባ ንዑስ ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳልካቸው ሞገስ የሽብር ቡድኑ በቀበሌው በቆየባቸው ቀናት የመንግሥት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ አውድሟል። ማኅበረሰቡንም በማስፈራራት እና በማስገደድ ጥሬ ገንዘብ፣ ምግብ እና መጠጦችንም በመዝረፍ ለከፋ ችግር መዳረጉን ነግረውናል። በዚህ የተማረረው ሕዝብም በአንድነት እየተፋለመው መኾኑን ነው ሥራ አስኪያጁ የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
Previous articleበአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር በካናዳ ሊካሄድ ነው።
Next articleበጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሠራተኞች ገንዘብ በማዋጣት ለወገን ጦር ስንቅ እያዘጋጁ ነው፡፡