የኩላሊት እጥበት ለማከናወን የሚረዳ ኬሚካል በሀገር ውስጥ ማምረት ሊጀመር ነው፡፡

248

የኩላሊት እጥበት የሚሠሩ ሆስፒታሎችን ቁጥር ከአንድ ወደ አራት ከፍ ለማድረግ ጥናት እየተደረገ ነው፡፡

ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2012 ዓ/ም (አብመድ) የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚዲካል ጀኔራል አቶ ያዕቆብ ሰማን ለኩላሊት እጥበት ሕክምና የሚረዳ ኬሚካልን ከሰኔ ወር ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት ቁሳቁስ የማስገባት እና የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለኩላሊት እጥበት የሚያገለግለው ኬሚካል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገባ ስለነበርና ከታማሚዎች ቁጥር ጋር የማይጣጣም በመሆኑ አገልግሎቱ ይቆራረጥ እንደነበር ጀኔራል ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ ለኬሚካሉ ቅመማ የሚያገለግሉ ንጥረ ነገሮች ከሀገር ውስጥ የሚዘጋጁና ከውጭ የሚገቡ እንዳሉም አመልከተዋል፡፡

የኩላሊት በሽታ ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ የእጥበት ሕክምና የሚፈልግ አጣዳፊ በሽታ ነው፡፡ ከእጥበት በኋላ ንቅለ ተከላ እንደሚያስፈልገውም ይነገራል፡፡ ይህን ለማድረግ ‹‹ሀገሪቱ በቂ ማሽኖች አሏት፤ ለሥራው እንቅፋት የሆነውን የኪሚካል እጥረት መፍታት ደግሞ የበርካቶችን ሕይወት ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል›› ብለዋል አቶ ያዕቆብ፡፡

ዘላቂ መፍትሔው እስከሚገኝ ከፍተኛ አገልግሎት በሚሰጡ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ዋና ዋና ሆስፒታሎች ለኩላሊት እጥበት የሚረዱ ማሽኖችን መሠራጨታቸውንም አቶ ያዕቆብ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

የኩላሊት ንቅለ ተከላን በብቸኝነት ሲያገለግል ከነበረው ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተጨማሪ ሦስት ሆስፒታሎች ለመክፈት ጥናት መድረጉንም ለአብመድ አስታውቀዋል፡፡ በአማራ ክልል በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስታሎች በጥናቶቹ ከተካተቱት ውስጥ እንደሆኑም ታውቋል፡፡

የኩላሊት በሽታ አጣዳፊ በመሆኑ የሦስቱ ሆስፒታሎች ሥራ የመጀመር ዕቅድ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለወራት እና ለዓመታት የሚወስደውን ወረፋ ከማስቀረም በላይ በርካታ ዜጎችን በወቅቱ ታክመው ሕይወታቸው እንዲተርፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡

የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ በሁሉም ክልሎች ውስጥ ያሉ ሆስፒታሎች ከዚህ በፊት እንደነበረው አገልግሎት መቆራረጥ እንዳይኖር የኬሚካል እና የቁሳቁስ ግዥ መፈፀማቸውን አቶ ያዕቆብ ተናግረዋል፡፡ ከፊታችን ጥቅምት ጀምሮ አገልግሎቶቹ እንዳይቆራረጡ ኬሚካሎቹ እንደሚያከፋፍሉም አስታውቀዋል፡፡

የኩላሊት እጥበት ኬሚካልን በሀገር ውስጥ በማምረት የተሳካ ንቅለ ተካላ የሚያደርጉ ሆስፒታሎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ እንደሆነ የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚዲካል ጄኔራል አቶ ያዕቆብ ሰማን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ 800 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የንፁሕ መጠጥ ውኃ እጥረት ችግር አለባቸው፤ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የንፅሕና አጠባበቅ ችግር ባለው የሕይወት ዘይቤ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ ለከፍተኛ የኩላሊት በሽታዎች ያጋልጣሉ፡፡ በታዳጊ ሀገራት በስፋት የሚስተዋል በሽታም ነው፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት የንፅሕና አጠባበቅ ችግሮች እና በንፁሕ መጠጥ ውኃ እጥረት ምክንያት በሚፈጠር የኩላሊት በሽታ በአንድ ዓመት ብቻ ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለሞት ይዳረጋሉ፡፡

የኩላሊት በሽታ ተያያዥ ለሆኑ የነርቭ ችግር፣ የስኳርና የደም ግፊት በሽታዎች ያጋልጣል፡፡ በእነዚህ በሽታዎች በዓመት የሚሞቱትን ቁጥር የኩላሊት በሽታ ከ19 ወደ 57 ሚሊዮን ከፍ እንደሚያደርገው በጥናት ተመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleየብሮድካስት ባለስልጣን የመገናኛ ብዙኃንን አስጠነቀቀ፡፡
Next articleየመገናኛ ብዙኃንን የሚቆጣጠረው አካል እንዲያርም ነዋሪዎች አሳሰቡ፡፡