
ሕዳር 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በዋግ ግንባር ተገኝተው የአካባቢውን የጸጥታ ኀይል ተቀላቅለዋል።
አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድንን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል የጸጥታ መዋቅሩ ብቻ ሳይኾን የክልል የሥራ ኀላፊዎች ግንባር በመሰለፍ መታገል እንዳለባቸውም ተገልጿል።
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ስዩም መኮንን በዋግ ግንባር ከሰሞኑ ነጻ በኾኑ አካባቢዎች ተገኝተው ለሚሊሻ አባላት እንዳሉት ለኢትዮጵያውያን አንድነት በተደረገው ተጋድሎ የዋግ ሕዝብም ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሏል፤ በርካታ ጀግኖችንም አፍርቷል። ይኹን እንጂ አካባቢው በከፈለው መስዋእትነት ልክ ተጠቃሚ አለመኾኑን ነው ያነሱት።
በተለይም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አካባቢውን ኾን ብሎ በመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዳይኾን የሠራው ተግባር ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህ ወቅት ደግሞ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በፈጸመው ወረራ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶችን እና የግለሰብ ሀብት እና ንብረትን ዘርፏል፤ መውሰድ የማይችለውን አውድሟል፤ ንጹሃንን ደግሞ በመግደል ለክልሉ ሕዝብ የነበረውን የቆየ ጥላቻ በገሀድ አሳይቷል ብለዋል።
ጠላት ይህንን ኹሉ አረመኔያዊ ድርጊት እየፈጸመ የሚገኘው ደግሞ የተለየ ብቃት ኖሮት ሳይኾን በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በሠራው የከፋፋይነት ተግባር የፈጠረውን ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መኾኑን አንስተዋል።

ይኹን እንጂ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሽብር ቡድኑን ሀገር የማፍረስ ዓላማ በመረዳቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነሳት አይቀጡ ቅጣት እየቀጣው መኾኑን ገልጸዋል። አቶ ስዩም የዋግ ሕዝብ እና ሚሊሻው የአካባቢውን ሰንሰለታማ ተራሮች እና ሸለቆዎችን እንደ ደጀን ተጠቅመው በሽብር ቡድኑ ላይ እያደረሱት ያለው ኪሳራ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል። የጠላት የተለመደ የሀሰት ፕሮፖጋንዳም በሕዝቡ ተቀባይነት እያጣ መምጣቱን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆን የሽብር ቡድኑን ብቻ ሳይኾን የውጭ ጋሻ ጃግሬያቸውን ጭምር ማሽመድመድ እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ስዩም የዋግ ሚሊሻ እና ሕዝብም የጀመረውን ትግል አጠናክሮ አካባቢውን ነጻ የማውጣት ታሪካዊ ግዴታ እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ