“ትናንት በታላቅ አዳራሽ ነበር የሚያጌጡ፤ ዛሬ ቀን ጥሏቸው እኩይ ሰው ገፍቷቸው በአመዱ ላይ ተቀመጡ”

232
ሕዳር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ቤት ነው መከተቻው፤ ቤት ነው ማጌጫው፤ ቤት ነው መዋቢያው፤ ቤት ዓለምን ማያው። አበው ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት ይላሉ። ዞሮ ዞሮ መግቢያው፣ ሲደክም ማረፊያው መክተቻው ቤት መሆኑን ሲያሳዩ። ቤት ዞሮ መግቢያ መሆኑን ሲያመላክቱ። አዱኛ ሲፈርስ ያሳዝናል። አንጀት ይበላል። እንግዳ የገበባት፣ ደስታ የታየበት፣ ልጆች የቦረቁበት፣ ወተት የተጠጣበት፣ ጠላና ፍርንዱስ የተቀዳበት ታላቁ አዳራሽ ሲፈርስ ምነዋ በደሌ ምኑ ላይ ይሆን? ያሰኛል።
ክፉዎች ክፉ ካላደረጉ አይተኙም። ካላሰናከሉና ሌላውን ካላሳዘኑ አያንቀላፉም። የተመቻቸ እንቅልፍ የሚወስዳቸው ደጎች ሲያለቅሱ፣ በሀዘን ሲላወሱ፣ የሌሎች ቤት ሲፈርስ ነው። ከራሳቸው ሰርግ ይልቅ በጎረቤታቸው ተዝካር ከበሮ ይደልቃሉ፤ እልልም እያሉ ይጨፍራሉ፤ ያጨብጭባሉ፤ ያሸበሽባሉ፤ ዳንኪራም ይመታሉ። ደስታቸው ክፉ ከማድረግ ጋር የተቆራኘች ናትና ክፉ ካላደረጉ አይስቁም፤ አይደሰቱምም።
በኢትዮጵያ ምድር ላይ የተነሱ ክፉዎች በንፁሐን ለቅሶ ስቀዋል፤ በእነርሱ የእንባ ብዛት ሃብት አካብተዋል። ጥሪት ሰብስበዋል። ከበደል ላይ በደል እየፈፀሙ መደሰትን መርጠዋል። ንፁሐንም ንፁሕ ልባቸው እየደከመች፣ እየተጎዳች፣ በመከራ ውስጥ ኖረዋል። ለዓመታት በሌሎች ለቅሶ ላይ የሳቀው፣ በሌሎች ተዝካር ቀን ከበሮ አንስቶ የደለቀው አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ዛሬም በንፁሐን ደም ላይ መሳቁን፣ መሳለቁን አላቆመም። ክፋትና ማጥፋት ከሌለ በምድር ላይ ተደስቶ መኖር አይቻለውምና ያለ ክፋት አያድርም።
አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በንፁሐን ኢትዮጵያውያን ላይ እልፍ በደሎችን ፈፅሟል። አሁንም የበደል እጁን አላጠፈም፤ የበደል ሰይፉን አልመለሰም። የሽብር ቡድኑ የአማራ ሕዝብ መከፋትና መገፋት ያስደስተዋል። ጥፋቱም ያረካዋል። በአማራ ሕዝብ ወረራ ፈፅሞ አማራን ገድሏል፤ አሰቃይቷል፤ ንብረታቸውን ዘርፏል፤ አውድሟል፤ ቤታቸውን አቃጥሎ በባዶ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።
አሁን ላይ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች እየተደመሰሰ ነው፤ ከመደምሰስ የተረፈውም ወደ ኋላ እየፈረጠጠ ነው። ታዲያ በፍርሃት እየሮጠም ክፉ ከማድረግ አይቦዝንም፤ እያጠፋ ይሸሻል እንጂ። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ተመትቶ በሸሸባቸው አካባቢዎች ተገኝቻለሁ።
በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ፤ በዚያ አካባቢ አያሌ ጥፋቶችን ፈፅሟል፤ በግና ፍየል ከጋጥ እየጎተተ እየወሰደ በልቷል፤ መሶብ እየገለበጠ፣ በርበሬና ሽሮ እየበረበረ አሟጧል፤ ጥሪት አልባ ይሆኑ ዘንድ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ከሁሉም ጥፋቱ ግን አንደኛው የበለጠ ልቤን አሳዝኗታል።
አመድ ላይ በሀዘን ኩርትም ብለው የተቀመጡ አባት አንጀቴን በሉት፤ ዳውድ ሙህዬ ይባላሉ። አርሶ መብላት፣ እንግዳ መጥራት፣ የደከመውን ማሳረፍ ነው የሚያውቁት። ለበቀል የሚያደርስ ክፉ ሥራ አልተገኘባቸውም። ሳይሰለቹ ማረስ፣ የተቸገረን ማጉረስ፣ የታረዘን ማልበስ ካልሆነ በስተቀር ክፉ የሚባል ሥራ አይገኝባቸውም። ውሏቸው ከማሳቸው፣ ከበሬዎቻቸው፣ ከአትክልታቸው ጋር ነው። የደከመ ጉልበታቸውን ሲያሳርፉም ከልጆቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ነው የሚገናኙት። መንገዳቸው እንዲሰላ፣ ቤታቸው አንዲሞላ ፈጣሪያቸው አሏህን ከመማፀን ውጭ ሌላ ለበቀል የሚያደርስ ሥራ አልተገኘባቸውም። ግን በደል ተፈፅሞባቸዋል።
አመድ ላይ ኩርትም ብለው ተቀምጠዋል፤ ሀዘን ውስጣቸውን አጥቁሮታል፤ አንጀታቸውን አሳርሮታል፡፡ ከተቀመጡበት ሥፍራ ላይ አያሌ ትዝታዎች አሉአቸው፡፡ ዛሬ ላይ አመድ የሆነው ቤታቸው ከአሁን በፊት የፍቅር ዘመን አሳልፈውበት ነበር፤ ጮማ የቆረጡበትን፣ ወተት የቀዱበትን፣ እንግዳ የተቀበሉበትን፣ ከልጆቻቸውና ከባለቤታቸው ጋር የተደሰቱበትን ያን መልካም ዘመን እያስታወሱ ከአመድ ላይ ተቀምጠው በሀሳብ ይምሰለሰላሉ።
በትዝታ ባሕር መስመጣቸው። ዳሩ ዛሬ ላይ ከትዝታ በስተቀር ምንም ነገር የላቸውም። ዙሪያቸው አመድ ብቻ ሆኗል። መግቢያ አጥተው፣ ከሰው ቤት ወድቀዋል። የትዝታ ማዕበል ወዲህና ወዲያ እያማታቸው ዝም ብለዋል። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በዚያ አካባቢ ወረራ በመፈጸም በደሎችንም ያደርስ ስለነበር ንፁሐን ተደናግጠዋል። ያን ቀን ባለታሪኩ እንዲህ ያስታውሱታል <<አሸባሪው መጣ መጣ ሲባል ልጆቼና ሚስቴ ተደናገጡብኝ። እኔም ለእነርሱ ብዬ አብረን ወደሌላ ቦታ ሄድን። እኔ ቤቱን እየተመላለስኩ አይ ነበር። አንድ ቀን ከዚያ ተመልሼ ስመጣ ቁም የት ልትሄድ ነው አለኝ። ምን አደርግ ብለህ ነው እኔ አርሶ አደር ነኝ አልኩት። በመሳሪያ አስፈራራኝ። ተመልሼ ሄድኩ። ዳግም እንዳልመጣ እንዳይመቱኝ ስለሰጋሁ በውጭ ተቀመጥኩ>> ቤታቸው ከመንገድ ጋር ዳር የተሠራ ነበር። በ
ዚያ ቀዬ ሲሻው እያስገደዱ እየተቀበሉ፣ ካለበለዚያ ቤት እየበረበሩ ዘርፍዋል። እኒህ የሽብር ቡድኑ አባላትም በእነ ዳውድ ሙህዬ ቤት ታዛ ንብ ይመለከታሉ። ሌላውን ዘርፈው አልበቃቸው ሲል ማሩን ቆርጠው በሉ፣ የቀረውን አወደሙ። ቤቱንም አቃጠሉ። <<ቤቴ እንዳለ አመድ ሆነ፤ በቤት ውስጥ የነበረ እህል፣ እቃ፣ ልብስ፣ የከብቶች ምግብ ሁሉም ወድሟል፤ ሁሉም ነው የነደደው።>> ነው ያሉን።
ቤታቸውን የሠሩት በ1990ዎቹ መጨረሻና ሰባ ቆርቆሮ የለበሰ ታላቅ አዳራሽ እንደነበርም ነግረውናል። አሁን ያን የመሰለ ወግና ማዕረግ ያዩበት፣ ያጌጡበትና የተደሰቱበት ቤት ተቃጥሎ እሳቸው አመድ ላይ ኩርትም ብለው ተቀምጠዋል። ያን የመሰለ ቤት በዚህ ዘመን የኑሮ ውድነት ከዬት አምጥተው ይተኩትና። አሁን ላይ አንጀታቸው እርር ብሎ ልጆቻቸውን የሚያስገቡበት አጥተው ተቀምጠዋል እንጂ።
ድሮ በቤታቸው የደከመ እንዳላረፈበት ዛሬ ላይ እርሳቸውም የሚያርፉበት አጥተዋል። ከባለቤታቸው ዘመዶች ተጠልለው እንደሚገኙም ተናግረዋል። <<በትክሻዬ ተሸክሜ ውኃ ያጠጣሁት አትክልትም እሳት በልቶታል። አንዲት ነገር አላወጣንም። ሁሉም ነው የወደመው። ንብን ሰበብ አድርገው ነው ያቃጠሉት ቤቴን። አሁን እሳት በሆነ ዘመን ምኑን ከምን አምጥቼ እገዘዋለሁ። እንዴት ብዬስ እሰረዋለሁ>> ነው ያሉት ዳውድ።
ታዲያ ቤተኞችን ያለቤት፣ ባለሃብቶችን ያለ ሃብት፣ ባለ ታሪኮችን ያለ ታሪክ የሚያስቀርን አጥፊ ቡድን እንዴት ተብሎ ዝም ማለት ይቻላል? እንዴት ይሆናል? ስንቶች ናቸው በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጥፋት እንባቸውን ያፈሰሱት፤ አንጀታቸውን በሀዘን ያላወሱት። በቃ ማለት አሁን ነው። ትናንት ከዚያ ወዲያ በታላቅ አዳራሽ ነበር የሚያጌጡ፤ ዛሬ ቀን ጥሏቸው እኩይ ሰው ገፍቷቸው ባመድ ተቀመጡ፡፡ ትናንትና ከዚያ ወዲያ በታላቅ አዳራሽ ያጌጡ የነበሩት አባት ዛሬ ላይ እኩይ ሰው ገፍቷቸው አዱኛቸውን ነጥቋቸው በአመድ ላይ ተቀምጠዋል። አቀማመጣቸው፣ አነጋገራቸው ሁሉ ያሳዝናል። ተሰናብቻቸው ወደ መጣሁበት አዘገምኩ። ሀዘናቸው፣ ህመማቸው፣ ቁስላቸው ግን እየተከተለኝ ነው።
በታርቆ ክንዴ
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
Previous articleበአዲሱ ፍኖታ ካርታ የተዘጋጀው የመማሪያ መጽሐፍ በመልካም ስብዕና፣ ክህሎትና ዕውቀት የተገነባ ትውልድን ለማፍራት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleበአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው፡፡