በአዲሱ ፍኖታ ካርታ የተዘጋጀው የመማሪያ መጽሐፍ በመልካም ስብዕና፣ ክህሎትና ዕውቀት የተገነባ ትውልድን ለማፍራት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

248
ባሕርዳር፡ ሕዳር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በነባሩ የትምሕርት ሥርዓት የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀው አዲሱ የመማሪያ መጽሐፍ በክልሉ ስድስት ዞኖችና በ30 የአንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምሕርት ቤቶች የሙከራ ትግበራ ተጀምሯል፡፡ 70 ሺህ 850 መጽሐፍት ለሙከራ ትግበራው ታትመዋል፤ በክልሉ በሚነገሩ አማርኛ፣ ኽምጣና፣ አዊኛ፣ ኦሮምኛና አርጎበኛ ቋንቋዎች መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
በአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ የሥርዓተ ትምሕርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ካሴ አባተ አዲሱ የመማሪያ መጽሐፍ ለሀገር በቀል እውቀት ትኩረት የሰጠ፣ ልዩ ፍላጎትና ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች የሚያበረታታ፣ የተግባቦት ክሕሎትን የሚያሳድግ፣ ለምርምር የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የትምሕርት ሥርዓቱ ችግር ፈች እና አራቆ አሳቢ፣ ወግ ባሕሉንና ታሪኩን የሚወድ፤ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በቀላሉ መረዳት የሚችል ትውልድ ለማፍራት ታስቦ መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ማተበ ታፈረ (ዶክተር) በዘላቂነት በትምሕርት ሥርዓቱ የተሟላ ስብእና ያለው ትውልድ ለመገንባት ለሙከራ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ላይ የማሻሻያ እና የእርምት ሀሳቦችን በመስጠት ተማሪዎች እና መምሕራን ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
አዲሱ የመማሪያ መጽሐፍት የሙከራ ትግባራ ከተጀመረባቸው ትምሕርት ቤቶች የባሕርዳር ከተማ አጼ ሠርፀ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኅብረተሰብ ሳይንስ መምሕር ተክለወልድ ብርሃኔ አዲሱ መጽሐፍ በነባሩ የትምህርት ሥርዓት የነበሩ የታሪክ አረዳድ፣ የሥነ-ምግባር፣ የሳይንስ እና ዕውቀት ክሕሎት ችግሮችን ሊፈታ እንደሚችል ተስፋ አድረገዋል፡፡ የሙከራ ትግበራውን ስኬታማ ለማድረግ ስልጠና መውሰዳቸውን የገለጹት መምሕሩ ለሙሉ ትግበራ እንዲበቁ የሚያግዝ እውቀት ማግኘታቸውንና ሥራውን ከተማሪዎቻቸው ጋር ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የሙከራ ትግበራው በዚህ ዓመት ተጠናቆ በ2015 የትምሕርት ዘመን በክልሉ ሙሉ ትግበራ ይጀመራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡-ባለ ዓለምየ
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
Previous articleበኩር ጋዜጣ ሕዳር 27/2014 ዓ.ም ዕትም
Next article“ትናንት በታላቅ አዳራሽ ነበር የሚያጌጡ፤ ዛሬ ቀን ጥሏቸው እኩይ ሰው ገፍቷቸው በአመዱ ላይ ተቀመጡ”