❝መከላከያ ሠራዊትን እና ልዩ ኀይልን መቀላቀል ለራስ ክብር፤ ለወገንም ኩራት ነው❞ የአማራ ልዩ ኀይል አባላት

185
ሕዳር 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እድሜ እና ሁኔታ የፈቀደለት ኹሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እና የአማራ ልዩ ኀይልን በመቀላቀል የሀገሩን ክብር ማስጠበቅ እና ሕዝቡን ከማንኛውም ጥቃት መከላከል እንዳለበት በጋሸና ግንባር የተሰለፉ የአማራ ልዩ ኀይል አባላት ተናገሩ። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የልዩ ኀይል አባላቱ የኢትዮጵያን አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ በኢኮኖሚ እንድትበለጽግ የማድረግ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ሀገርን ለማጽናት መመረጥ ትልቅ ዕድል ነው። የተገፋን ሕዝብ ነጻ ማውጣት ኩራት ነው። ስለ ሀገር መወለድ፣ ለአንዲት ሰንደቅ ዓላማ ጸንቶ መኖር፣ ለሕዝብ ነጻነት በክብር መሞት ታላቅ ክብር ነው። ታዲያ ከመለዮ ለባሽ በላይ ክብር ያለው ማን አለ?
በጋሸና ግንባር የተሰማራው የአማራ ልዩ ኀይል ከሌላ የወገን ጦር ጋር በመሆን አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ድባቅ እየመታ ነው። የጠላትን ምሽግን እየደረመሰ፣ ጠላትን እየደመሰሰ፣ የወገኑን አንጀት እያራሰ፣ በድል እየገሰገሰ፣ ሕዝቡንም ነጻ እያወጣ ያለ ጀግና ሠራዊት ነው። ይህ ኀይል የአባቶቹን ታሪክ ለማስጠበቅ እየተፋለመ አዲስ ታሪክ እየሠራም ይገኛል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የልዩ ኀይል አባላት በተለይ በዚህ ጊዜ መለዮ ለብሶ ስለ ሀገር መፋለም ትልቅ ክብር አለው ብለዋል።
ረዳት ሳጅን ሀብታሙ ደርሶ የልዩ ኀይል አባልነት መለዮ ለባሽ በመሆኑ የተለየ ክብር እንደሚሰማው ተናግሯል። የተገፋን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር የልዩ ኃይል አባል በመሆኑ ሁልጊዜ ደስተኛ እንደሆነም አንስቷል።
እንደ ሻማ ቀልጦ ሀገር እና ሕዝብን ነጻ ከማውጣት በላይ ክብር የለም ያለው ደግሞ ረዳት ሳጅን ኪሮስ በቀለ ነው።
ሌላው አባል ኮንስታብል ታደሰ ጀምበር በተለይ በዚህ ጊዜ የሠራዊቱ አባል መሆን ታሪክ ለመሥራት መመረጥ ነው ብሏል። የማትደፈር ኢትዮጵያን እና የተከበረ ሕዝብ የሚኖርባትን ሀገር ለማቆየት የሠራዊቱ ሚና መተኪያ እንደሌለውም አስገንዝቧል።
የልዩ ኀይል አባላቱ “የምንኖርላት ሀገራችን ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ጠንካራ አደረጃጀት ያለው የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ያስፈልጋታል”ብለዋል። ለዚህም ወጣቱ በመከላከያ ሠራዊት እና በልዩ ኀይል ተደራጅቶ መዘጋጀት አለበት ነው ያሉት። የልዩ ኀይል አባላቱ እንዳሉት “ሀገር ለማስከበር እና ሕዝብን ለመታደግ መዘጋጀት ለራስ ክብር፤ ለሀገርም ኩራት ነው። እድሜው የደረሰ ወጣት ሁሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እና ልዩ ኀይሉን ተቀላቅሎ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለመውሰድ እና ሕዝብን ከማንኛውም ጥቃት ለመታደግ ዝግጁ መኾን አለበት” ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ – ከጋሸና
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
Previous articleወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ጥሪ አቀረበ፡፡
Next articleበሎስ አንጀለስ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል 640 ሺህ ዶላር ተሰበሰበ።