
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የህልውና ዘመቻው አሰባሳቢ ግብረ ኀይል በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሠጥቷል፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እና የህልውና ዘመቻው የገንዘብ አሰባሳቢ ግብረ ኀይል ሠብሳቢ አቶ አማረ ሠጤ የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በጥሬ ገንዘብ እና በዓይነት የሚሠበሰበው ድጋፍ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አማረ እንዳሉት ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በርካታ ውድመቶችን አድርሷል፤ ማኅበረሰቡም የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በሚደረገው ርብርብ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡ እስካሁንም ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከከተማ ነዋሪው፣ ከአርሶ አደሩ፣ ከመንግሥት ሠራተኞች፣ በክልሉ ካሉ የልማት ድርጅቶች እና ሠራተኞች፣ ከፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከክልሉ ቢሮዎች እንዲሁም ከዲያስፖራው 3 ቢሊየን 320 ሚሊዮን 55 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
ምክትል አፈ ጉባኤው እና የህልውና ዘመቻው የገንዘብ አሰባሳቢ ግብረ ኀይል ሠብሳቢ አቶ አማረ የሽብርተኛውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ስንቅ ለማቅረብ 67 ሺህ 52 ኩንታል ስኳርን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች፣ 56 ሺህ 837 ካርቶን ብስኩት፣ 10 ሺህ 179 ሰንጋዎች፣ 178 ሺህ 585 ደርዘን ጁስ እና ውኃ ከማኅበረሰቡ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን የከፈተብንን ጦርነት ለመቀልበስ ሁሉም ኀላፊነቱን በትጋት መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
አቶ አማረ ጦርነቱን በድል የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በገንዘብ እና በዓይነት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክልሉ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ሕዝብ ተፈናቅሎ ይገኛል ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤው ነፃ በወጡ አካባቢዎች መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ተፈናቃዮችን ለመመለስ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት ርብርብ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ በባንክ ከተከፈቱ አካውንቶች በተጨማሪ በተከፈተው የቴሌ ኤስ ኤም ኤስ 9595 ገቢ በማድረግ መደገፍ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorpora