
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የዓለም አቀፍ መገናኛ አውታሮች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተዛባ መልኩ እየዘገቡ እንደሆ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ የውጭ መገናኛ ብዙኀን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተዛቡ መረጃዎችን ለማሰራጨት ከሚጠቀሙባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው የሰብዓዊ እርዳታን በተመለከተ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ምክንያት ወደ ትግራይ ሊገባ የሚችለውን እርዳታ ማስተጓጎሉን ማንሳት አይፈልጉም፤ በአየርም ሆነ በምድር መንግስት ለትግራይ ክልል ድጋፍ ለማድረስ የሚያደረገውን ጥረትም መዘገብ ዓይፈልጉም ነው ያሉት፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህ የሚያሳየው ዓላማቸው ሌላ መሆኑን ነው ብለዋል፡፡
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አማካኝነት በአማራና በአፋር ክልሎች ሚሊዮኖች ተፈናቅለው በርካቶች ህይወታቸውን አጥተው እነዚህን አሰቃቂ ሁነቶች አለመዘገብ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ግልጽ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ሲ ኤን ኤን ባለፈው አንድ ዓመት ሲዘግብ የነበረው አጀንዳ ጅምላ ጭፍጨፋ የሚል የተሳሳተ መረጃ ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህ ፍጹም ስህተት መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር የተሳተፈበት የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ትናንት የትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል እንዲሰበስቡ ማሳሰቡን ተከትሎ ቢቢሲ ያወጣው ዘገባ ተማሪዎችን ለጦርነት ማቀጣጠያ እያደረገ ነው በሚል ዓለምን አሳስቷል ሲሉም የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኀን እያስተላለፍት ያለውን የተሳሳተ መረጃ አስገንዝበዋል፡፡
ይህ የኢትዮጵያውያንን ውቅር ካለማወቅ የመነጨ እንጅ ተማሪዎች ሰብልን ሲሰበስቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም ነው ያሉት፡፡ ባህላችንና የማንነታችን አንድ አካል የሆነውን ተግባር ለዓመታት ስንተገብረው የቆየን እንጅ አዲስ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡
በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ጉዳዮች እንደ ሀገር ራሳችንን ለመቻልና ነጻነታችንን ለማስጠበቅ ለውጭ መገናኛ ብዙኀን የተሳሳተ ዘገባ ጀሮ ሳንሰጥ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ለፖለቲካ ዓላማ የኢትዮጵያን እውነታ ሲሸፋፍኑ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን የሀገራቸውን እውነታ ለዓለም በማስረዳት ኀላፊነታቸውን እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡
በደጀን አምባቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation