የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች አካባቢያቸውን ተደራጅተው በንቃት እየጠበቁ ነው።

223
ሕዳር 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሽብርተኛው ትህነግ ከበትረ ሥልጣኑ እስኪወገድ ድረስ እንደ ማንኛውም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ነዋሪዎች የዳንሻ ከተማ አስተዳደር አማራዎችም ማንነታቸውን ክደው እንዲኖሩ ከፍተኛ የጭቆና ቀምበር ተጭኖባቸው ነበር። ታሪክ አዋቂ የኾኑና ለመብታቸው ሲሟገቱ የነበሩ አማራዎች በጨካኙ ቡድን እየተሳደዱ ተገድለዋል፤ የራሳቸውን አካባቢ ትተው እንዲሰደዱም ተደርገዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች በ2007 ዓ.ም የበጎ አድራጎት ማኅበር ቢመሰርቱም ፈቃድ ይከለከሉ ነበር። “እናንተ የአማራ ወጣት ብቻ ኾናችሁ ነው የተደራጃችሁት፤ መወያየትም ኾነ መደራጀት አትችሉም” በማለት የማኅበሩን አባላት ሲያሳድዷቸው፣ ሲያስፈሯሯቸውና ሲያንገሏታቸው እንደነበረ ቀሪዎቹ የቡድኑ አባላት ይናገራሉ። ይኹን እንጂ ያለ ቦታውና አካባቢው በሕዝብ ላይ ጭቆናን ሲያደርስ የነበረው አረመኔ ቡድን በተባበረ ክንድ ከሥልጣኑም ኾነ የማያውቀውን አካባቢ ለቅቆ እንዲጠፋ ተደርጓል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ዳግም የጭቆና ቀምበሩን በሕዝብ ላይ ሊጭን ቢፍጨረጨርም ወረራ በፈጸመበት አካባቢ ኹሉ እንደ በጋ ቅጠል #እየረገፈ ይገኛል። እንደ ወርቅ ተፈትኖ እዚህ የደረሰው ጎዶሊያስ የዳንሻ ከተማ አስተዳደር በጎ አድራጎት የወጣቶች ማኅበር ተስፋ የቆረጠው አሸባሪው ቡድን ከተማቸውን እንዳያውክ 24 ሰዓታት ነቅቶ በመጠበቅ የቡድኑ ሰርጎ ገቦችን አንገት እያነቀ ለሕግ እያቀረበ ነው። ወጣቶቹ በየተራ በመኾን እንቅልፍ ሳይተኙ ከፀጥታ አካላት ጋር በመኾን የአካባቢያቸውን ደኅንነት እየጠበቁ ይገኛሉ።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የጋዜጠኞች ቡድን ወጣቶቹ በየኬላው ጥብቅ ፍተሻ ሲያደርጉ ለመመልከትም እድሉን አግኝቷል። የማኅበሩ አባል የኾነው ወጣት ደሳለኝ ጫኔ ከፀጥታ አካላት ጋር በመኾን ጠላት ሰርጎ እንዳይገባ በየ ኬላው ከፍተኛ ቁጥጥር እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግሯል። በኬላ ብቻ ሳይኾን በከተማዋ በመዘዋወር ሰርጎ ገቦችን የመፈተሽ ተግባር እያከወኑ እንደሚገኙ የተናገረው ወጣቱ እስከ አሁን ባደረጉት የጠላት ሰርጎ ገቦችን ለፀጥታ አካላት ተላልፈው መስጠታቸውንም አስረድቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከበትረ ሥልጣኑ እንዲገረሰስ ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ትግል ሲያካሂዱ እንደነበረም አስታውሷል።
ሌላዋ የማኅበሩ አባል ወጣት እህትነሽ ትዛዙ ሽብርተኛው ትህነግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በማንነቷ ብቻ ሲያስራትና ሲያንገላታት እንደነበረ ተናግራለች። በተለይ በዓላት ሲደርሱ የሚፈልጉትን የባህል አልባሳት እንዳይለብሱና እንዳያጌጡ፣ የሚፈልጉትን ሙዚቃ እንዳያዳምጡ ጫና ሲደርስባቸው እንደነበረ ነው ወጣቷ ያስታወሰችው። አኹን የነፃነትን አየር እያጣጣሙ እንደሚገኙ የተናገረችው ወጣቷ ሰርጎ ገቦች ሽብር የመፈጸም እድል እንዳያገኙ ጠንክረው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጻለች።
አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን #ለማጥፋት እየተደረገ ለሚገኘው የህልውና ዘመቻ የማኅበሩ አባላት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እያደረጉ እንደኾነም ገልጻለች። ቡድኑ ወረራ ከፈጸመበት አካባቢ ኹሉ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስም ሴትና ወንድ ሳይሉ ጠንክረው እንደሚታገሉ ወጣቷ አረጋግጣለች።
ወጣት ዓለሙ ጌታቸው ከሚያደርጉት የፍተሻ ተግባር በተጨማሪ የማኅበሩ አባላት ወደ ግንባር ለመዝመትም ዝግጁ መኾናቸውን ተናግሯል። “በደማችንና በላባችን ያገኘውን ነፃነት እንዲለመልም እናደርጋለን” ነው ያለው።
ጎዶሊያስ የዳንሻ ከተማ አስተዳደር በጎ አድራጎት ወጣቶች ማኅበር አስተባባሪ አድማስ ጌታቸው ማኅበሩ ሲመሰረት አሸባሪው ትህነግ የተፎካካሪ ፓርቲ አባል ናችሁ በማለት የተለያየ እንግልት ሲፈጽምባቸው እንደነበረ አስታውሷል።
በከተማዋ የሽብርተኛው ትህነግ የዘወትር ተግባር ማኅበሩ የሚፈርስበትን መንገድ መፈለግ እንደነበረም ወጣቱ ጠቁሟል።
ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ያሳለፈው ማኅበር አኹን በአማራ ክልል መንግሥት እውቅናን አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ እንደኾነም አስተባባሪው አስረድቷል።
ማኅበሩ ከሚያካሂደው የሰርጎ ገቦች ፍተሻ በተጨማሪ፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ ሕፃናትና በሽብር ቡድኑ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች በተደጋጋሚ ድጋፍ እንዳደረጉ ተናግሯል። የማኅበሩ አባላት በየወቅቱ የከተማዋን ጽዳት እንደሚጠብቁም ነው አስተባባሪው የተናገረው።
የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሥልጣን አድማሴ በከተማዋ ጠንካራ ፍተሻ እየተከወነ መኾኑን ተናግረዋል። የከተማዋ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመኾን ሰርጎ ገቦችንና ተላላኪ ባንዳዎችን እያጠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል። የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች ወደ ግንባር በመዝመት፣ በተደጋጋሚ ስንቅ በማዘጋጀት ጠንካራ ደጀንነታቸውን እያሳዩ እንደኾነ ከንቲባው አስረድተዋል። ጠላትን ታግሎ በመጣል፣ የከተማን ደኅንነት በመጠበቅም ኾነ ወደ ግንባር በመዝመት የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ተሞክሮን ማስፋት እንደሚያስፈልግም አቶ ሥልጣን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ-ከዳንሻ ከተማ
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
Previous article“ቃርሚያ መልቀም”
Next articleዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ለፖለቲካ ዓላማ የኢትዮጵያን እውነታ ሲሸፋፍኑ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን የሀገራቸውን እውነታ ለዓለም በማስረዳት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ጠየቀ፡፡