የጋሸና የጨለማ ወራት…

184
ሕዳር 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጋሸና ወደ ከተማ አስተዳደርነት ከተሸጋገረች ወደ ስምንት ወራት ገደማ ሆኗታል። ታዲያ ሕዝቡ ደስታውን አጣጥሞ ሳይጨርስ ጥቁር መጋረጃ ተጋረጠበት። ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም በውድቅት ሌሊት ከተማዋን በግፍ የወረረው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል። በርካታ ንጹሐን ሰዎች ተገድለዋል፣ሴቶች ተደፍረዋል። በግለሰቦች ቤትም ከሻይ ብርጭቆ ጀምሮ እስከ ትላልቅ ንብረቶች ተዘርፈው ወደ ትግራይ ተጭነዋል።
የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተዘርፈዋል፤ ወድመዋልም። ለዘጠኝ ወረዳ መጋቢ የሆነ ሰብስቴሽን ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የጋዜጠኞች ቡድን በከተማዋ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ባንኮች ከመዘረፋቸው ባለፈ የሥራ መሣሪያዎቻቸው አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ ተሰባብረዋል። የሕክምና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የኤሌክትሪክ አውታሮች፣ የመጠጥ ውኃ መሠረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንም የጋሸና ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ መላኩ ወረታ ተናግረዋል።
አቶ መላኩ እንዳሉት የጋሸና ከተማ እና አካባቢዋ ሕዝብ አሸባሪውን ቡድን ለመፋለም ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ከወገን ጦር ጎን ተሰልፎ ሲታገል ቆይቷል። የወገን ጦር በወሰደው ጠንካራ የማጥቃት ርምጃ ከተማዋ ነጻ ወጥታለች፤ ከተማዋን ለቅቆ የነበረው ሕዝብ እየተመለሰ ሲኾን በነጻነት መንቀሳቀስ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
ከተማዋ ነጻ ከወጣች በኋላም ነዋሪዎቹን ለቀጣይ ትግል የማነሳሳት እና ወጣቶችን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። የቀጣይ ተግባራትን በመለየትም ከተማዋን ወደነበረችበት ለመመለስ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተስፋሁን ባታብል ሕዝብን አንገት በማስደፋት ሀገር ለማፍረስ የተንቀሳቀሰው አሸባሪ ቡድን ያደረሰው ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥፋት መቼውንም ቢሆን የአማራን ሥነልቦና አይጎዳም ብለዋል። በተወረሩ አካባቢዎች የነበረውን ከፍተኛ ተጋድሎ በማሳያነት አንስተዋል። ችግር ውስጥ የከረመው የጋሸና ሕዝብ ቤት ያፈራውን ይዞ ለወገን ጦር ፍቅሩን መግለጹም በተወረሩ አካባቢዎች ያለው ሕዝብ እኛን እየጠበቀ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
አይደፈሬው የወገን ጦር ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች የዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ሥምሪት መሰጠቱንም አመላክተዋል። እንደ ዋና አስተዳዳሪው ማብራሪያ የወደሙ ንብረቶች መረጃ ማጣራትና ማኅበረሰቡ ከጠላት ሸሽጎ ያስቀመጣቸውን ንብረቶች ማደራጀት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት ናቸው።May be an image of indoor
ችግሩ አንገት የምንደፋበት ሳይሆን ኢኮኖሚያችንን በአጭር ጊዜ የሚያገግምበት፣ ማኅበረሰቡ ያጋጠመውን ችግር የሚጋፈጥበትና የተቋረጡ ሥራዎች በፍጥነት የሚጀመሩበት ይሆናል ነው ያሉት። “ይህ ወራሪ ቡድን ከክልሉ ወጥቶ ከሄደ ተመልሶ ጠላት መኾኑ አይቀርም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በተወረሩ አካባቢዎች ጠላት እንዳይሸሽ የሽምቅ ውጊያው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መደረጉን ገልጸዋል። ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ጠላት ከገባበት እንዳይወጣ፣ የዘረፈውን ሀብት እንዳያሸሽም ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ -ከጋሸና
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
Previous articleአዲስ አበባ በአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት መገናኛ ብዙኃን እንደሚወራው ሳይሆን ሰላሟን አረጋግጣ የቀጠለች ከተማ ናት ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር አውሮሊያ ካርባሎ ተናገሩ።
Next article“ቃርሚያ መልቀም”