
ሕይወታቸው ካለፉት ውስጥ ሰባት ነፍሰጡር ፣ አምስት ሕጻናት እና ሰባት ደግሞ ተመላላሽ ታካሚዎች ናቸው ተብሏል፡፡
ሕዳር 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እኩይ ድርጊቱን ቀጥሎበታል፡፡ አሸባሪው ቡድን በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በፈጸመው ወረራ ንጹሐንን ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ ንብረት ዘርፏል፤ አውድሟል፡፡ ቡድኑ ካወደማቸው አንዱ የአምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ይጠቀሳል፡፡
የአምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ብርሃኑ ዓለሙ እንደተናገሩት ሆስፒታሉ ከተመሰረተ ጀምሮ ያከማቻቸው የሕክምና መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶች እና ሌሎች ግብዓቶች በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በመውደማቸው በሆስፒታሉ ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ 19 ሰዎች ሕክምና አጥተው ሕይወታቸው አልፏል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሰባት ነፍሰጡር፣ አምስት ሕጻናት እና ሰባት ተመላላሽ ታካሚዎች መኾናቸውን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በሆስፒታሉ ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል። ሆስፒታሉ ከ150 ሺህ በላይ ሕዝብ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱም ተገልጿል፡፡
ሕይወታቸውን ካጡ ተመላላሽ ታካሚዎች ውስጥ የ25 ዓመቷ ወጣት እምወዳት አሰፋ አንዷ ነበረች። ወጣቷ ለአራት ዓመታት ያህል በልብ ድካም እና የደም ግፊት ህመም ተጠቂ ኾና ቆይታለች። በአምደወርቅ ሆስፒታልም ክትትል ስታደርግም ነበር። ወጣቷ በሐኪሞቿ ክትትል ይደረግላት ስለነበር በመልካም ጤንነት ላይ ትገኝ እንደነበር የሟች ታላቅ እህት ወይዘሮ አስቴር ነግረውናል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአካባቢው ወረራ ሲፈጽም አንዱ የጥቃት ዒላማው በርካቶች የሚገለገሉበትን የህክምና ተቋማት መዝረፍና ማውደም ነበር፡፡ በዚህም ጉዳት የደረሰበት የአምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት አቆመ፡፡ በሆስፒታሉ የህክምና ክትትል ስታደርግ የቆየችው እምወዳት ህመሟ በመባባሱ ለህልፈት መዳረጓን ታላቅ እህቷ ወይዘሮ አስቴር ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በሆስፒታሉ ባደረሰው ውድመት እህቷን በማጣቷ ልቧ እንደተሰበረ የተናገረችው ወይዘሮ አስቴር ከዚህ በላይ የሚመጣ ጉዳት ስለማይኖር የሽብር ቡድንን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል ኹሉ ለመሳተፍ መዘጋጀቷን ገልጻለች።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
