በጎንደር ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ ተጀምሯል።

227

የፀጥታ ኃይሉ ከከተማው ማኅበረሰብ ጋር ሆኖ የሠላም መስከበር ተግባር እያከናወነ መሆኑን ከተማ አስተዳድሩ አስታውቋል፡፡

ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2012 ዓ/ም (አብመድ) አብመድ በከተማዋ ተንቀሳቅሶ እንደተመለከተው በጎንደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የንግድ ማዕከላት፣ የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው። መደበኛ እንቅስቃሴው ተቀዛቅዞ የነበረው የአዘዞ ክፍለ ከተማ ትናንት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መግባቱንም ተመልክተናል፡፡

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ በሪሁን ካሰው ለአብመድ እንደተናገሩት አንዳንድ በሕግ የሚፈለጉ ግለሰቦችን ለመያዝ እየተሠራ ባለበት ጊዜ የተወሰነ የሠላም መደፍረስ በክፍለ ከተማው ተከስቶ ነበር። በዚህ ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ የተወሰነ መደናገር በመፈጠሩ የአገልግሎት መቋረጥ ተከስቶ ቆይቷል።
ይህንን ችግር ለመፍታት ከወጣቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ተካሂዶ የተዘጉ አገልግሎት ሰጪ ታቋማትም እንዲከፈቱ ተደርጓል።

ትናንት ማምሻውንም መደበኛ እንቅስቃሴው መቀጠሉን ምክትል ከንቲባው ነግረውናል። ከጎንደር – መተማ እና ከጎንደር – ሳንጃ ተቋርጦ የነበረው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴም እንዲሁ መደበኛ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡ የፀጥታ ኃይሉም ከከተማው ማኅበረሰብ ጋር ሆኖ የሠላም መስከበር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ይፋ አለመሆኑ የስነ ልቦና ጫና እንደፈጠረባቸው ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
Next articleየብሮድካስት ባለስልጣን የመገናኛ ብዙኃንን አስጠነቀቀ፡፡