❝የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በመረዳት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት መገንዘብ መቻላቸው ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው❞ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ

155
ሕዳር 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል እና ግብረአበሮቹ በኢትዮጵያ ላይ የሚያቀርቡት የጅምላ ጭፍጨፋ እና ረሃብን ለጦርነት የመጠቀም የክስ ጫጫታ ከእውነት የራቀ ሰለመሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ባከሄዱት የጋራ ምርመራ ሪፖርት ማስታወቃቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል፡፡
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በሳምንታዊ መግለጫቸው በዲፕሎማሲው ዘርፍ ስኬቶች የተመዘገቡበት እንደነበር አንስተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው የቻይና አፍሪካ የንግድ ፎረም ላይ የተገኙ ውጤቶችን ሲገልጹ አፍሪካውያን ያለ ቀረጥ ወደ ቻይና የግብርና ምርቶቻቸውን ለመላክ እንዲችሉ ቃል መገባቱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች የግብርና ውጤቶች በመሆናቸው የተገኘው እድል ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዩ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በመረዳት ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሯን በራሷ የመፍታት አቅም ያላት መሆኗን መገንዘብ መቻላቸው ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን የተመራው ልኡክ በሴኔጋል ዳካር በመገኘት ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በማስገንዘብ በዲፕሎማሲው በኩል ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
የበቃ ወይም #NoMore ዘመቻ መጠናከር፣ አርቲስቶች እና ታዋቂ ሰዎች መሳተፍ መቻላቸው በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ለመቀልበስ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
ለህልውና ዘመቻው የሀብት ማሰባሰብ ሥራውም ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመላክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አንድ አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዓላትን በሀገራቸው ተገኝተው እንዲያከብሩ ጥሪ መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡
የዓለም አንዳንድ ትልልቅ ተቋማት ኢትዮጵያን ሲከሱበት የቆዩት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተለይም የጅምላ ግድያና ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል የሚል ክስን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሸን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሸን ባደረጉት የጋራ ምርመራ በቀረበው ሪፖርት መሰረት ምንም አይነት ረሀብን ለጦርነት የመጠቀምና የጅምላ ግድያ ሪፖርት አለመቅረቡን አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው እንዳሉት አንዳንድ ኤምባሲዎች የአዲስ አበባ የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በማስመሰል የሚያናፍሱት ወሬ ከአሉባልታ የተነሳ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዛሬም ሰላሟ የተጠበቀ እንደሆነ ገልጸው የማንኛውም ሀገር ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ በሰላም ገብቶ የመንቀሳቀስ እና የመጎብኘት እድሉ የተጠበቀ እንደሆነ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ደጀን አምባቸው
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
Previous articleከኢፌዴሪ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በሳምንታዊ መግለጫቸው ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች፡፡
Next article“…በአንድነት ተነስተን አሸባሪዎችን ድባቅ እንመታለን” ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ