
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ ኦባላ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በኢትዮጵያ በቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ዜጎችን ለከፋ ችግር መዳረጉን በአገኘው አጋጣሚ አብራርቶላቸዋል።
በጋምቤላ ክልል የተወለደውና በአሜሪካ ሚኔሶታ ኦስቲን የምክር ቤት አባል የሆነው ኦባላ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመሰረተ ልማት ጉዳዮች ላይ ባተኮረው ስብሰባ ንግግር አድርገው ሲወጡ በአካል አግኝቶ አነጋግሯቸዋል።
በዚህ ወቅትም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በኢትዮጵያ በቀሰቀሰው ወረራ ምክንያት ኢትዮጵያውያንን ለከፋ ችግርና ስቃይ መዳረጉን ገልጾላቸዋል።
ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር በነበረው ቆይታ በተወለደበት ጋምቤላ ከዚህ ቀደም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከተጠነሰሰ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተርፎ መውጣቱን እንደገለጸላቸው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ አስታውቋል።
ከዚህ ባለፈም ሽብርተኛው ትህነግ በሥልጣን ዘመኑ አኝዋኮችን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰባቸውን ሰቆቃ በተመለከተም ማስረዳቱን ይገልጻል። በወቅቱም ፕሬዚዳንቱ የተሰማቸውን ሃዘን እንደገለጹለትም ነው በጽሑፉ ያሰፈረው።
በተጨማሪም በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የግጭት ሴራ እስካሁን ድረስ መላው ኢትዮጵያውያን እያሳለፉትና እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ በተመለከተ እና አሜሪካም ይህን ሽብርተኛ ቡድን መደገፍ እንደሌለባት ማብራራቱንም ጠቁሟል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation