
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር እንድትወጣ በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ መደገፍ እንዳለባቸው የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ጥናት መምህር ሙሉነሽ ደሴ ተናገሩ፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራ እና በአፋር ክልሎች ባደረገው ወረራ በርካታ ንጹሃንን ገድሏል፤ ቀሪዎቹን ከሞቀ ቤታቸው አፈናቅሎ ለስደት ዳርጓቸዋል፤ ሃብታቸውን ዘርፏል፤ አውድሟል፡፡ በኃይል በወረራቸው አካባቢዎች መሠረተ ልማቶችን በማውደም የሰዎችን መኖሪያ ቀዬ እንዳልነበር አድርጓል፡፡
የሽብር ኃይሉን እንቅስቃሴ ለማስቆም እና ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዲፕሎማሲው እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ተገቢውን እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ በተለያዬ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለሀገራቸው ዲፕሎማት መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
መምህር ሙሉነሽ እንደተናገሩት ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ማድረግ ሌላው ሊያከናውኑት የሚገባ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ጦርነቱን ተገዳ የገባችበት መሆኑን፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ያላት ሀገር መሆኗን፣ ለባርነት የማትንበረከክ ሀገር መሆኗን ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ወራሪዎች በተለያየ ጊዜ በግፍ ቢወሯትም ሽንፈትን ያላስተናገደች ይልቁንም ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሆነች ሀገር መሆኗን ማስረዳት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የውጭ ሀገራት ለባርነት ቢያጯትም ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ አጥንት እና ደም ፀንታ የቆመች፣ ለዘላለም በማይነቃነቅ መሠረት ላይ አንድነቷን የገነባች ሀገር መሆኗን ለሚኖሩበት ሀገር ሕዝብ እና መንግሥት ማስረዳት የዘወትር ተግባራቸው መሆን እንዳለበትም መክረዋል፡፡
መምህር ሙሉነሽ እንዳሉት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገራቸው መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በወረራቸው አካባቢዎች የወደሙ መሠረት ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከመንግሥት እና ከሕዝቡ ጎን ሊቆሙ ይገባል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳይገጥማት ወደ ሀገር ውስጥ የሚልኩትን ገንዘብ በሕጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ በመላክ፤ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሰማራት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ድጋፍ በማድረግ፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ ሠፊ ተሳትፎ በማድረግ ከሕዝቡ ጎን በመቆም አብሮነታቸውን ሊያስመሰክሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ