“አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አሁናዊ እጣፈንታው ተከቦ መቀጥቀጥ ብቻ ሆኗል” በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምሕር

191
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የአማራ እና አፋር ክልሎችን በመውረር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያቀደው ቅዠት በወገን ጦር እየተወሰደበት ባለው እርምጃ እየመከነበት መኾኑን ዛሬ እንኳን በተገለጸው የድል ዜና መገንዘብ ይቻላል፡፡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በተለይም ሚሌን እና ጭፍራን መያዝ አለመቻሉ አቅሙ የምላሱን ያህል አለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ነው፤ የጋሸና ስትራቴጅካዊ ምሽጎቹ በጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ፣ ሚሊሻና የክተት ዘማቾች መሰበሩ ሌላኛው ኪሳራው ነው፡፡
በወቅታዊ ጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምሕርና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የኾኑት አቶ ያሬድ አያሌው እንደገለፁት ጋሸና በወታደራዊ ሳይንስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ገዢ ቦታ ነው፡፡ የወገን ጦር በአሁኑ ወቅት ጋሽናን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ ቀጣይ ለሚወስደው እርምጃ እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጋሸናን መልቀቁ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ትልቅ የድል ብስራት መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ መምሕሩ እንደተናገሩት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአፋር በኩል ሚሌ እና ጭፍራ እንዳይደርስ ተደርጓል፤ በደብረ ሲና እና ጣርማ በር ሲያደርገው የነበረው ጉዞም በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ብርቱ ክንድ የተዘጋ ነው፤ ይህም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ተከቦ መቀጥቀጥ ብቻ ሆኗል አሁናዊ እጣ ፋንታው፡፡
አቶ ያሬድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር መዝመት ሁሉን ነገር ቀይሮታል ብለዋል፡፡ የጋሽና ምሽግ ተሰበረ ማለት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ይበታተናል፤ የተበታተነውን እየተከተሉ መደምሰስ ነው፤ እንደ ሀገር በቀጣይ ቀናትም የሚገኘውን ድል በጉጉት እድንጠብቅ አድርጎናል ብለዋል፡፡
የተገኘውን ድል ተከትሎ በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረው መነቃቃት እጅግ የሚገርም ነው ያሉት አቶ ያሬድ “አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ተሸንፎ ሲወጣ ሕዝቡ እጅግ በተደራጀ መንገድ ሊደመስሰው ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ያሬድ እንዳሉት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ሲገባ በርካታ በደሎችን እያደረሰ ገብቷል፤ ሲወጣ ግን ከዚያም የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፤ በመኾኑም በወረራ በተያዙ አካባቢዎች ያለው ኅብረተሰብ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የመጨረሻ እና ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ላይ መድረሱን አውቆ ራሱን በንቃት ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም በተጀመረው የማጥቃት እንቅስቃሴም የወገን ጦርም በፍጥነት እየደረሰለት መኾኑን ተገንዝቦ በጋራ በመኾን ጠላትን መፈናፈኛ ማሳጣት ይገባዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ” የሌላቸው አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትም ከተሸናፊ ጋር ቆመው ስለማያውቁ አሸናፊ ከኾነው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ጋር መቆማቸው አይቀሬ ጉዳይ መሆኑን ምሁሩ ተናግረዋል፡፡ ምዕራባውያን ሀገር ሲነካ ከጫፍ ጫፍ የተነሳውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እያስመዘገበ ያለውን ታሪካዊ ድል በተግባር እያዩት ነው፤ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና መላ የአፍሪካ ሀገራት እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦም ኢትዮጵያ እውነትን ይዛ የተነሳች፣ ማሸነፍም የሚገባት መኾኑን የሚያሳይ ሲሉ ገልጸውታል፡፡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የሁሉም ጠላት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በጋራ ከነ አስተሳሰቡ ሊቀብሩት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
Previous articleየአማራ ሕዝብ የዘረፈውን እና ወገኑን የገደለውን ጠላት እንዲሁ ሊያሳልፈው እንደማይገባ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ አሳሰቡ፡፡
Next articleበውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሀገራቸውን በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ በመደገፍ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡