የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ይፋ አለመሆኑ የስነ ልቦና ጫና እንደፈጠረባቸው ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

583

ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2012 ዓ/ም (አብመድ) የጎንደርና የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎቹ ተማሪ ቤተልሄም ወንድዬ እና ምስራቅ ተጫነ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስገባቸውን ውጤት አሟልተው የምደባ ቦታቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ነገር ግን በትምህርት ዘመኑ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ምደባ ይፋ አለመሆኑ የስነ ልቦና ጫና እንዳሳደረባቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ የተመደቡበትን የትምህርት ተቋም ሳያውቁ እንደ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ያሉት ተቋማት የመግቢያ ቀናትን ቆርጠው አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች ጥሪ ማስተላለፋቸው ተገቢ አለመሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳሬክተር ዶክተር ዳዊት አስራት ተማሪዎች እንዲገቡ ጥሪ የተላለፈው ዩኒቨርስቲያቸው ከጠራበት ቀን በፊት ትምህርት ሚኒስቴር ምደባውን ይፋ ያደርጋል በሚል እሳቤ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ለቀጣይም አዲስ ተማሪዎች ከምደባ በኋላ እንዲገቡ በማስታወቂያ እንደሚነገር፣ ነባር ተማሪዎች ግን በተጠቀሰው ቀን መግባት እንደሚጠበቅባቸው ዶክተር ዳዊት አስረድተዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ምደባው የዘገየው ከምደባው በፊት መሰራት ያለባቸውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መተግበር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፤በቅርብ ቀናትም ይፋ ይደረጋል ብሏል፡፡ ቀኑን ግን በግልፅ አላሳወቀም።

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

Previous articleበጥናት ላይ የተመሰረተ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድና ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleበጎንደር ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ ተጀምሯል።