የአማራ ሕዝብ የዘረፈውን እና ወገኑን የገደለውን ጠላት እንዲሁ ሊያሳልፈው እንደማይገባ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ አሳሰቡ፡፡

201
ባሕርዳር፡ ሕዳር 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮ ኀላፊው አቶ ግዛቸው ለሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ለሰሜን ሸዋ ነዋሪዎች መልእክት አስተላልፈዋል
አቶ ግዛቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ በየተሰለፉባቸው ግንባሮች እያስመዘገበው ባለው ድል የጠላት ኃይል ለሳምንታትና ለወራት ከነበረባቸው ይዞታዎች በወገን ጦር እየተመታ ሲሆን ከምት ያመለጠው ደግሞ ሾልኮ ለማምለጥ እየሞከረ ይገኛል ነው ያሉት።
የጠላት ኃይል ለወራት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች “ከተሸነፍን አጥፍተናችሁ ነው የምንሄደው” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ከአሸባሪውና ወራሪ ኃይል በተደጋጋሚ ያደርሳቸው እንደነበር ነው የገለጹት።
ከዚህም በተጨማሪም ጠላት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ሽንፈት ሲደርስበት ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ ማካሄድ የሚታወቅበት ባህሪው ስለሆነ ማኅበረሰባችን የወገን ጦር አካባቢዎችን እስኪቆጣጠር በቀያችሁ ያለውንና የሚሸሸውን የጠላት ኃይል ተዘጋጅታችሁና ነቅታችሁ በመጠበቅ ራሳችሁን ከድንገተኛ ጥቃት መከላከል እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
ራስንና ቤተሰብን ከድንገተኛ ጥቃት መከላከል እንደተጠበቀ ሁኖ ጠላት ዘርፎ የሚያጉዘውን ሀብት ማስቆም እንዲሁም መንገዶችን በድንጋይ፣ በእንጨት እና ሌሎች ዘዴዎች በመዝጋትና በመቁረጥ እንቅስቃሴውን እንድትገቱ እንጠይቃለን ብለዋል አቶ ግዛቸው።
ወራሪው ኀይል ይዟቸው በቆየባቸው አካባቢዎች ለሳምንታትም ሆነ ለወራት መሰረቱን ለማስፋትና ቦታዎች በወገን ቁጥጥር ሥር ሲውሉ ግድያ ለመፈጸም በህቡእ የተደራጁ የአሸባሪ ቡድኑ ህዋሶች ከማኅበረሰቡ ጋር በማመሳሰል ጥሎ ሊሄድ ስለሚችል ህዝባችን ለወገን ጦር ጥቆማ በመስጠትና ለሚመለከተው በማሳወቅም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባው ነው የተናገሩት።
በእነዚህ አካባቢዎች የአሸባሪው ቡድን አባላት ለወራትም ሆነ ለሳምንታት ያደረሱትን ግድያ፣ መፈናቀልና የሀብት ውድመት የምንረሳው ሊሆን አይገባም። ይህ ኃይል ወገኖቻችንንና ልጆቻችንን የገደለ፣ ሴቶቻችንን የደፈረ፣ ሀብት ንብረታችን ያወደመ እና እንደ ህዝብ የአማራን ህዝብ ለማዋረድ አስቦ ሲሰራ የቆየ ኃይል ነው። ስለሆነም በተጠቀሱት አካባቢዎች የምትገኙ ወገኖቻችን ይህ የጠላት ኃይል ነገም ተመልሶ እንዲወረንና ጉዳት እንዲያደርስብን ልንፈቅድ አይገባም ብለዋል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኀላፊው።
በመሆኑ ጠላትን የመቅበርና ውጦ የማስቀረት ሥራውን በአግባቡ ልንወጣ ይገባል። አንድም ንብረት ከአካባቢያችን እንዳይወጣ ተደራጅተን መሥራት እና ጠላትን በገባበት ማስቀረቱ እንደተጠበቀ ሁኖም ጠላት የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስና በህዝባችን ላይ ተጨማሪ ጉዳቶችን ለማድረስ የሽብር ቡድኑ አባላት ራሳቸውን በመቀየር ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሰርገው ለመግባት ጥረቶች ስለሚኖሩ ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት መቆጣጠር እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
Previous articleአይደፈሬው የወገን ጦር በጋሸና ግንባር አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ይተማመንበት የነበረውን ምሽግ ደርምሶ ጠላትን ድባቅ እየመታ ነው።
Next article“አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አሁናዊ እጣፈንታው ተከቦ መቀጥቀጥ ብቻ ሆኗል” በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምሕር