
ሕዳር 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለወገን ጦር እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል። እናቶች ለኢትዮጵያ ክብር፣ ለኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ጭቆናን ለማጥፋት፣ ነፃነትን ለማምጣት እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል። እናቶች ልጆቻችን በድል ሳይመለሱ፣ ኢትዮጵያም ሰላም ሳታገኝ ስንቅ ከማዘጋጀት ወደኋላ አንልም እያሉ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም እናቶች ልጆቻቸው ወደ ዘመቱበት ዘምተው እንደሚዋጉ፣ ካልሆነም የኮዳ ውኃ እንደሚያቀብሉ፣ ቢወድቁ እንደሚያነሱ ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን በመካነ ሰላም ከተማ ስንቅ ሲያዘጋጁ ያገኘናቸው እናቶች የስንቅ ዝግጅታቸው ሠራዊቱ የቆመበትን ዓላማ ከግብ እስኪያደርስ ድረስ ይቀጥላል ብለዋል። ጠላት ካልተደመሰሰ፣ ሠራዊቱም በድል ካልተመለሰ በስተቀር ዝግጅታቸውን እንደማያቋርጡም ነው ያስረዱት።
ለሠራዊቱ ስንቅ ሲያዘጋጁ ያገኘናቸው ወይዘሮ ጀማነሽ አራጋው የሕልውና ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ ለሠራዊቱ የሚያስፈልገውን ስንቅ እያዘጋጁ ሲልኩ መቆዬታቸውን ነግረውናል። እርጅና ተጫጭኖኝ ነው እንጂ እየሸለልኩ እና እየፎከርኩ ሄጄ ግንባሩን ማለት ተመኝቼ ነበር ነው ያሉት። ‟አሁን እርጅናዬን እየወቀስኩ ነው፣ የአርበኛ ልጅ ነኝ፣ ማይጨው የዘመተ አባት አለኝ። ልዝመትም ብዬ ነበር አርጅተሻል ተብዬ እንጂ፣ ውኃ ማቀበል አይሳነኝም ነበር፣ እዛው ሄጄ ምራቄን ዋጥ አድርጌ ለኢትዮጵያ ሀገሬ ጀብድ ብሠራ ደስ ይለኝ ነበር። ወላሂ አሁንማ እልህ እያከሳኝ ፣ እያመነመነኝ መጣ” ሲሉም ቁርጠኝነታቸውን ነግረውናል።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ከአሁን ቀደም አታሎ ሲገዛ እንደኖረ የተናገሩት ወይዘሮ ጀማነሽ አሁን ደግሞ ሕዝብ ሊጨረሱ ሲነሱ ለሀገሬ ለኢትዮጵያ ጀማነሽ አራጋው ሄዳ ጀብድ ሠራች ብባል ጀሃድ ይሆንልኝ ነበር ብለውናል። ሥንቁን ማዘጋጀት እንደማያቆሙ እና ድል እስከሚገኝ ድረስ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት። ‟በሬ የሚስበው በአንጀቱ እንጂ በአንገቱ አይደለም። በሬ ካልበላ አይስብም። እነርሱም ቢሆን ውኃ ሲጠማቸው አለው ብሎ ካላጠጧቸው፣ ሲርባቸው ካላጎረሷቸው ድል አይገኝም። እኛ ጦም ውለን አድረን እነርሱ ቢበሉልን ነው ምኞታችን ብለዋል። ሁሉም ታጋይ ነው“ብለዋል ወይዘሮ ጀማነሽ።
አብዛኛው ሰው ያለውን ለመስጠት የተዘጋጄና ጀግና ታጋይ መሆኑንም ተናግረዋል። ትግላቸው እንደማይቆምም ገልፀዋል። እርጅናን ወደዬት በጣልኩት ሲሉም ይቆጫሉ። ‟ማሸነፋችን የታወቀ ነው፣ ሌባ ምንጊዜም ይሠርቃል እንጂ አያሸንፍም። የወሬ ቦንብ አይምታችሁ፣ የወሬ ቦንብ ሲፈነዳ ሀገራችሁን አትልቀቁ፣ ለሌባ በር ከፍታችሁ አትልቀቁ” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

እናቶች ‟ ጀግናው ልጅሽ ድል አረገልሽ። ወታደሩ እና ጠረፍ ጠባቂው አንተ ነህና“ እያሉ እንደቀድሞው ሁሉ ልጃቸውን እየመረቁና ስንቅ እያስያዙ መላክ አለባቸው። እኔም አብሬ ብጓዝ ደስ ይለኝ ነበር። እርጅና መጣ እንጂ ‟ለሀገር ጥሪ የሄደው ልጅሽ፣ ድል አረገልሽ” እያልን እንከተላቸው። እኔም እንዲሁ እያልኩ ሠራዊቱን ብከተለው የደከመው ይበረታ ነበር ነው ያሉት። እኔም ከተፈቀደልኝ እሄዳለሁ፣ አቅም ያላቸው ይሂዱ ልጆቻቸውን ያበረታቱ፣ ልጆቼ ኢትዮጵያ ማሸነፏ አይቀሬ ነው፣ አላህም አደራ አለበት፣ ማንም ይምጣ ኢትዮጵያን አያሸንፍም፣ ለኢትዮጵያ እረኛዋ ብዙ ነው፣ ጠላት በያለበት እልም ይላልም ብለዋል።
ሌላኛዋ እናት ወይዘሮ የሺህወርቅ አርጋው ሥንቅ ማዘጋጀቱ ለእኛ ቀላል ነው፣ ዝመቱ ብንባልም እንዘምታለን፣ ስንቅ እናቀብላለን የወደቀ እናነሳለን ነው ያሉት። ሀገራችን አማን እስኪሆን ድረስ በዱዓውም፣ በጉልበቱም አለን፣ ወደኋላ አንልም ብለዋል። ጠላት ሸክሙን ከላያችን ላይ አላወርድልን ብሎ ተሸክመነው ኖረናል ያሉት ወይዘሮ የሺህወርቅ ሸክሙ ከላያቸው ላይ እስኪወርድ ድረስ ትግላቸው እንደሚቀጥልም ገልፀዋል። ‟የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ አንተኛ፣ ያለንን ነገር እንስጥ፣ አንድ እንጀራ እንበላ እንደሆነ ግማሹን ለእነርሱ፣ አንድ ጀሪካን ውኃ እንጠጣ አንደሆነ ግማሿን ለእነርሱ እያልን ትግሉን እንቀጥል ሀገራችን ሰላም እስኪሆን ድረስ፣ ወደ ኋላ አንበል፣ እንበርታ“ ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

አቶ የሱፍ ገዛኸኝ ጠላት በአማራ ክልል ገብቶ የሕልውና ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ ስንቅ ሲያቀርቡ መቆዬታቸውን ገልፀዋል። ኅብረተሰቡ አይዟችሁ በርቱ እያለ ሠራዊቱን እንደሚያበረታታም አስታውቀዋል። የሚሰበሰበው ስንቅ በሕዝቡ ፍላጎትና ተነሳሽነት መሆኑንም አስረድተዋል። እድሩ ለድጋፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። ጠላት ከምድረ ገፅ እስኪጠፋ ድረስ ድጋፋችን ይቀጥላል ነው ያሉት። ከስንቅ ዝግጅት ባለፈ ወጣቶች ወደ ዘመቻ እንዲሄዱ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልፀዋል። እየተደራጁ አካባቢያቸውን እየጠበቁና ተፈናቅለው በከተማቸው የሚገኙ ዜጎችን እየተንከባከቡ መሆናቸውንም ነግረውናል።
የሀብት አሰባሳቢ ኮምቴ ሰብሳቢ ኢብራሂም በዜ የመንግሥት መዋቅሩን ከእድር መዋቅር ጋር በማስተሳሰር ሀብት ሲያሰባስቡ መቆዬታቸውንም ገልፀዋል። አማራን አጥፍቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣን ኀይል ሕዝባዊ በሆነ መንገድ የመታገል ኀላፊነትም ግዴታም አለብን ብለዋል። የከተማዋ ማኅበረሰብ በተለያየ አደረጃጀት በመግባት እያገዘ መሆኑንም ነው ያብራሩት። ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ በአግባቡ እየደገፈ መሆኑንም ተናግረዋል። ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ