
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ-ካናዳዊያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 100 ሺህ የካናዳ ዶላር መሰብሰቡን አስታውቋል።
የኢትዮ-ካናዳዊያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶክተር) ወደ ጦር ግንባር በመዝመታቸው በእጅጉ ኮርተናል ብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስተሩን መዝመት ተከትሎ ”በውጭ የምንኖር በምን ልናግዝ እንችላለን” በሚል ኢክናስ ባደረገው ስብሰባ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ገንዘብ አሰባስቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ችግር ተጋፍጣ በአሸናፊነት የምታልፍበት ወሳኝ ወቅት ላይ በመሆኗ እኛም የድርሻችንን እንወጣ በሚል ውይይቱ መካሄዱ ታውቋል።
በዚህም በስብሰባው ላይ የተገኙ ዳያስፖራዎች ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል100 ሺህ የካናዳ ዶላር የለገሱ ሲሆን በቀጣይም በየወሩ ቋሚ እርዳታ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮ-ካናዳዊያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) ገንዘቡን በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ አስታውቋል።
ድርጅቱ በካናዳ የሚኖረው ዳያስፖራ በማስተባበር ለተቸገሩ ወገኖች ተጨማሪ እርዳታ ማሰባሰቡን እንደሚቀጥል ገልጿል።
”ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነትና ፍቅር አሁን ካለችበት ፈተና ትሻገራለች፤ እኛም ይህን እውን ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን” ብሏል።
የኢትዮ-ካናዳዊያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) ከተቋቋመበት ሕዳር ወር 2013 ዓ.ም እስካሁን ለወቅታዊ ጥሪና ለልማት ፕሮጀክቶች 278 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ መርዳቷን አመልክቷል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation