
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2012 ዓ/ም (አብመድ) ወጣቶች የተከሰተውን የሰላም እጦት ለመፍታት ያደረጉት ርብርብ የሚያስመሰግን መሆኑን የክልሉ ሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ አስታውቋል፡፡
በጎንደር ከተማና አካበቢው እንዲሁም የጸጥታ ችግር በተከሰተበት ጭልጋ እና አካባቢው የተፈጠረውን የሰላም እጦት አስመልክቶ የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ዛሬ መስከረም 22/2012 ዓ.ም ጎንደር ላይ ከወጣቶች ጋር መክረዋል፡፡ በምክክራቸውም ወጣቶች የከተማውን ሰላም ለማስጠበቅ ያደረጉት ተሳትፎ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል። ግጭቱ በአማራ እና በቅማንት ማኅበረሰብ መካከል የተፈጠረ አለመሆኑን ይልቁንም በ“ጽንፈኛ” የቅማንት ኮሚቴዎች እና በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት መከሰቱን ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ግጭት ፈጣሪዎች የክልሉን ሰላም በማይፈልጉ አካላት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ነው አቶ አገኘሁ የተናገሩት፡፡
የሰላም መደፍረሱን ለማስቆምም የወጣቶች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ሚና የጎላ ነበር ብለዋል። ምንም እንኳን ሰላም ለማስጠበቅ ሌሊት እና ቀን የሚሰሩ ወጣቶች ቢኖሩም የክልሉን ሰላም የማይፈልጉ አካላትን አጀንዳ እየተቀበሉ የሚያስፈጽሙ አካላት መኖራቸውንና አጀንዳ ተቀባይ የተባሉት አካላትም የሚቀየስላቸውን ስልት ሁሉ ከመከተል ወደ ኋላ እንደማይሉ ወጣቱ ሊረዳው እንደሚገባ አሳስበዋል።
‘ልዩ ኃይልን በአካባቢው እንዲኖር አንፈልግም’ የሚል አካሄድ ከመርህ ያፈነገጠ ተግባር መሆኑን በመግለጽ የክልሉ የጸጥታ አካላት በየትኛውም የክልሉ አካባቢዎች ሰላም የማስጠበቅ እና የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኳቸውን እንደሚፈጽሙ አስገንዝበዋል፡፡ ሰሞኑን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እና ጥፋተኞችን ከሕዝቡ ነጥሎ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድም ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
በጎንደር እና አካባቢው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የኅብረተሰቡ በአንድነት መጓዝ ብቸኛ አማራጭ መሆኑን የገለጹት የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊው ወጣቱ የሰላሙ አምባሳደር ሆኖ ከሰራ ችግር ሊፈጠር እንደማይችል አስገንዝበዋል፡፡ የተዘጉ መንገዶችን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ማስከፈት፣ በህገ ወጦች ላይ በማስረጃ ላይ ተመስርቶ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ፣ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እና የሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ በቀጣይ የሚሰሩ ተግባራት መሆናቸውን አቶ አገኘሁ አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ ተግባርም ወጣቶች ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ይሆናል ብለዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች እና የኅብረተሰብ ክፍሎችም የከተማዋን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከሰሞኑ የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት የከተማው ወጣቶች ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው የሰሩት ውጤታማ ሥራም እንደማሳያ ተነስቷል። ግጭቱን የሕዝብ በማስመሰል የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ የግል እና የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ፤ ከክልሉ ውጭ ሆነው ጥብቅና የቆሙ እና ለግጭቱ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትንም የክልሉ መንግስት ጊዜ ሳይሰጥ ማስቆም እንዳለበትም ወጣቶቹ አንስተዋል።
በክልሉ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በጎንደር ከተማ መረጃ እያቀበሉ ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት መፈተሸ እንዳለባቸውም የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ ወጣቶቹ አጠራጣሪ ነገሮችን ለመንግስት ቢያሳውቁም በመንግስት መኩል ፈጠኖ መረጃዎችን መጠቀም ላይ መዘግየት እንደሚስተዋልም ነው የተናገሩት፡፡ ከክልሉ ውጭ ሆነው ግጭት የሚያባብሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የክልሉ መንግስት ጠንከር ያለ አቋም ይዞ እንዲሰራም ጠይቀዋል።
አቶ አገኘሁ በሰጡት ምላሽ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት በጥናት ላይ የተመሰረተ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድና ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ወጣቶች፣ ፋኖዎች፣ልዩልዩ አደረጃጀቶች እና ባለሀብቶችም ተባባሪ እንዲሆኑ አሳስበዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ወጣቶችም በየአካባቢያቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ነው ውይይቱ የተጠናቀቀው፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ