
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከቅድመ ክርስቶስ ልደት በፊት በቀጣናው ገናን እና ከግብጽ ደቡባዊ ግዛት እስከ ህንድ ውቅያኖስ የሚደርስ ማንነት እና ግዛት የነበራት ታላቅ ሀገር እንደነበረች የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ፡፡ የተወሰኑትን እንኳን ብንጠቅስ ከክርስቶስ ልደት በፊት 1 ሺህ አንድ መቶ ዓመታት በላይ የነበረው ዳዊት በመዝሙሩ ኢትዮጵያ ብሎ የሚጠቅሳት ሀገር ጠንካራ እና የተደራጀ ሥዓርተ መንግሥት እንደነበራት እውቁ የታሪክ ተመራማሪ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ያስረዳሉ፡፡
ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ9ኛው መቶ ዓመት የነበረው ሆሜር ኢሊያድ እና ኦዲሰይ በተሰኙ የጽሑፍ ሥራዎቹ በእስያ ጠረፍ የነበረችውን የትሮይ ከተማ ለማስመለስ በተደረገው ውጊያ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በታላቅ ጀግንነት መዋጋታቸውን ይጠቅሳል፡፡ በዚሁ ዘመን ገደማ ኢትዮጵያውያኖቹ ለጦርነት ሲጓዙ የብረት ሰረገላዎችን ይጠቀሙ እንደነበር ድሩሲላ ዱንጂ ሒውስተን 1926 (እ.አ.አ) መጥቀሷን ጌታቸው ተስፋዬ 2003 ዓ.ም ይነግረናል፡፡ የወቅቱ ኢትዮጵያ በሚል ስም የሚታወቀው ግዛት እና ሕዝብ ጨዋ፣ ታታሪ፣ ባለጸጋ፣ ስልጡን፣ ጀግና እንደነበር ነው የታሪክ ድርሳናቱ ያሰቀመጡት፡፡
የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው ሄሮደተስ (ከክርስቶስ ልደት በፊት 425 ገደማ) ‹‹ላይኛውን ዓባይ የሚቆጣጠሩ ብልህ ሰዎች፣ ዕድሜአቸው የረዘመ፣ ባህላቸው፣ ሥርዓታቸው እና ሥነ ምግባራቸው በወርቃማው ዘመን ሰዎች የተመሰለ፣ በዓላቶቻቸውና ግብዣዎቻቸው የራሳቸው የሆነ የተከበሩ ነበሩ›› ሲል ኢትዮጵያውያንን በአድናቆት ገልጿቸዋል፡፡

የኢትዮጵያዊያን ታላቅነትና ገናናነት እየቀጠለ አክሱም ዘመነ መንግሥት ላይ ይደርሳል፡፡ ከወቅቱ ነገሥታት ለአብነት የሚጠቀስ የንግስተ ሳባ እስራዔል ድረስ የተዘረጋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ በግዙፍ የንግድ ትስስር በዓለም ዝናው የናኘ እና በወታደራዊ ብቃቱ ጠንካራ ነበር፡፡ በወቅቱ ታምሪን የተባለ ገናና ኢትዮጵያዊ ነጋዴም እስከ 120 የንግድ እቃ የሚጭኑ ግመሎች (ወርቅ፣ እጣን፣ የዝሆን ጥርስ፣ ወዘተ ናቸው የወቅቱ ሸቀጦች) እና 73 ያህል የንግድ መርከቦች እንደነበሩት ክብረ ነገሥት ገጽ 13 ላይ ተጽፎ እናገኛለን፡፡
ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 1980 የህንድ ንጉሥ ራማ ኢትዮጵያን ለመውረር ጦር ሰብቆ መጣ፤ በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያኑ የዮቅጣን ልጆች ከያሉበት ተጠራርተው ንጉስ ራማን እስከ መግደል የደረሰ የጦር ሜዳ ጀብድ በመፈጸም ሀገራቸውን ነጻ አውጥተዋል፡፡ (የኢትዮጵያ የ5 ሺህ ዓመታት ታሪክ፤ ከኖህ አስከ ኢህአዴግ፤ ፍስሐ ያዜ ካሳ 2003 ዓ.ም ገጽ 55-56).
ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ነጻነት ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ባሕር ተሻግሮ፣ ሀገር አቆራርጦ ተገፋ ከሚሉት ሕዝብ ጎን ለመቆም ከላይ የትሮይኑን ግዙፍ ጦርነት ለአብነት አንስተናል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላም ይህ ዓይነቱን ክስተት እናስተውላለን፤ ለአብነት ንጉሥ ካሌብ (485 እስከ 515 ዓ.ም) በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የሚኖሩ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በአይሁዳውያኑ ይደርስባቸው የነበረውን ጭፍጨፋ ለመከላከል 72 ታላላቅ መርከቦችን እና 70 ሺህ ወታደሮችን አዝምተው ነበር፡፡ (ፍስሐ ያዜ ካሳ፤ ገጽ 117 -118).
በታሪክ ቅኝታችን ዘመነ መሳፍንትን ስንመለከትም ከ1777 እስከ 1845 ዓ.ም ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪክ መሳፍንቱ ገብር አልገብርም በሚል እርስ በርስ ይሻኮቱ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ የኀይል ፉክክራቸውም የጋራ ጠላት ወረራን ለመመከት የሚያስችላቸው የጦር ልምምድ ለማድረግ ረድቷቸዋል፡፡ (እዚህ ጋ ከውጭ በሃይማኖት ስብከት ስም የሚመጡ የውጭ ዜጎች እና በጥቅም የሚገዟቸው ባንዳዎች ለነገሥታቱ የዕርስ በርስ ሽኩቻ አቀጣጣይ ነበሩ).

ከላይ የጠቀስናቸውን የኢትዮጵያን ጥልቅ እና ጥንተ ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ (1847-1860 ዓ.ም) የኢትዮጵያን ግዙፍ ታሪክ እና ዝና በማሳነስ የመከፋፈሉ እና በየመንደሩ የመሻኮቱ ጉዳይ ማብቂያ ሆኑ፡፡ የዘመነ መሳፍንቱ ነገር አበቃ፡፡ “ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን” የሚል መርህ ይዘው እስከ እየሩሳሌም ድረስ የማስገበር ህልም ሰንቀው ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ያላቸውን የጸና አቋምም መቅደላ ላይ ራሳቸውን በመሰዋት በተግባር አረጋገጡ፡፡
ሌላኛው ኢትዮጵያዊያን በዓለም ታላቅነታቸውን፣ አልደፍር ባይነታቸውን፣ ጀግንነታቸውን፣ ያስመሰከሩበት ታሪክ ታላቁ የአድዋ ጦርነት ነው፡፡ የካቲት 23 /1888 ዓ.ም የአድዋ ድል- አፍሪቃ በአጠቃላይ በአውሮጳውያን ቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ በወደቀችበት ዘመን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ፣ ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀችበት ልዩ ድል ነው። አድዋ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያሰባሰበ፤ የጥቁር ሕዝብ ድልም ነው፡፡
የታሪክ ፕሮፌሰሩ ራይሞንድ ዮናስ የአድዋ ጦርነት፤ በዘመነ ቅርምት የአፍሪቃ ድል በተሰኘው ድንቅ መጽሐፋቸው በወቅቱ በሚገርም ሁኔታ በሚገባ የተደራጀ ግዙፍ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዓለም ታሪክ የማይታሰበውን ፈጽሟል፤ በወራሪው የጣሊያን ጦር ላይ በመትመምም የጣሊያን የአፍሪቃ ቅኝ ግዛት የጦርነት ወረራንም ድባቅ መትቷል፤ ምሕረት አልባ በነበረው የአውሮጳውያን መስፋፋት ኢትዮጵያ ነጻነቷን በተሳካ መልኩ አስጠብቃለች ሲሉ ነበር የገለጹት፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ጣሊያን በ1927 ዓ.ም ዳግም የተጠናከረ የበቀል ወረራ ብትፈጽምም ኢትዮጵያውያን የሚቀመሱ አልሆኑም፡፡ አሁንም ነጭ ዳግም ኢትዮጵያን ለወረራ እንዳያስብ አድርገው ሸኝተውታል፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ዛሬም ስማቸው ሲወሳ ይኖራል፡፡
የኢትዮጵያውያን የጦርነት ወርቃማ ድል የታሪክ ቅኝት ሲነሳ የኮርያ ዘማቾችን ገድል በጥቂቱም ቢሆን ማንሳት ግድ ይላል፡፡ ከዛሬ 72 ዓመታት በፊት በኮሪያ ጦርነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሰኔ 19/1942 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ አሥራ ስድስት የዓለም ሀገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ስፍራው ለመላክ ወሰነ፡፡ ከነዚህ ሀገራት መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአምስት ዙር 6 ሺህ 37 ወታደሮችን አዝምታለች። ኢትዮጵያውያኑ የቃኘው ሻለቃ አባላት በኮሪያ ምድር ከዘመቱ ተዋጊዎች ሁሉ የተሰጣቸውን ሁሉንም ግዳጅ በድል የተወጡ ብቸኛ ወታደሮች ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ከተሳተፉ ሀገራት መካከል ሁሉም በጠላት እጅ የወደቁ ምርኮኛ እስረኞች ሲኖሯቸው ኢትዮጵያ አንድም ምርኮኛ እስረኛ ያልነበራት ብቸኛ ሀገር ናት፡፡

“አይዞሽ አሞራ አይዞሽ ጭልፊት
ቃኘው ሻለቃ አልፏል ከፊት”
“አጨደው ከመረው ወቃው እንደ ገብስ፤
የኢትዮጵያ አርበኛ ኮሪያ ድረስ” ተብሎም ተገጥሞላቸዋል፡፡
የቃኘው ሻለቃ ዘማች አባላትን ሰሜን ኮሪያዎች እንደ ልዩ አይቀመሴ ፍጡር ያዩአቸው ነበር፤ እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን “ኢትዮጵያውያን እልኸኞች ናቸው፤ መማረክን አይቀበሉም፤ ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም፤ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ህልማቸው ነው፤ ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ” በሚል አድናቆት ነበር የገለጻቸው፡፡
ጉንደት (1876 ዓ.ም) እና ጉራዕ (1876 ዓ.ም)፣ የካራ ማራን (የካቲት 26 /1970 ዓ.ም)፣ በውጭ ሀገራት ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ አሁንም ድረስ ሱዳን አብዬ ግዛት… የኢትዮጵያውያን ወታደሮች ወርቃማ ድሎች ማንሳት ምን ብእር ምን ቃላት፣ ምን ጊዜስ ሊበቃ…
ሜጀር ጄኔራል ሁሴን አህመድ ‹መስዋእትነት እና ፅናት (1997 ዓ.ም)› በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ኃይሎች አመሰራረት በአጼ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና ዘመን ነው የጀመረው፡፡ በዚህ ወቅትም የሆለታ ገነት እና የሐረር ወታደራዊ እና የደብረ ዘይት አየር ኃይል ማሰልጠኛዎች ሥራ ጀመሩ፡፡ በ1944 ዓ.ም በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥር ተደራጅተው ራስ አበበ አረጋይ የመጀመሪያው የጦር ሚኒሰቴር ሆኑ፡፡
እንደ ሜጀር ጄኔራል ሁሴን ማብራሪያ የወቅቱ ወታደር የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን ለማስከበር እና የጦር ግዳጁን ለመፈጸም ቃል ኪዳን በገባው መሰረት በኦጋዴን በረሃ በቀን በሀሩር ሌት በቁር ዘብ ቆሞ ነበር፤ በኬንያ ጠረፍ በዶሎ እና በሞያሌ፣ በሱዳን ድንበር በቃሮራ፣ በተሰነይ እና በመተማ በንቃት ጠመንጃውን አንግቶ፣ ጀበርናውን በጀርባው ተሸክሞ፣ የብረት ባርኔጣውን ደፍቶ፣ የጥይት ዝናሩን በወገቡ ታጥቆ በንቃት ሀገሩን ይጠብቅ ነበር፡፡ በምጽዋ እና በአሰብ የሀገርን ድንበር በንቃት በመጠበቅ ረገድ ጀግኖቹ የባሕር ኃይሉ እና አየር ኃይሉ ኀላፊነት የጎላ ነበር፡፡ ድህረ 1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተለያየ አደረጃጀቶችን በመከተል በተለይ የዚያድባሬን ወረራን በጀግንነት መክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በጠላት የማትደፈር መሆኗንም ያረጋገጠ ሌላናው ድል ነበር፡፡
የቀድሞዎቹ ጀግኖች የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የዛሬውን ሽብርተኛ ቡድን ትህነግን ከአመሰራረቱ ከጥንተ የባንዳነት ታሪኩ ጀምሮ ጠንቅቀው ያውቁታል፤ ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነው ቡድንም ጀግኖቹ አይደፈሬ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቃል፤ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ታሪክ የማይረሳው ገድል ፈጽመዋልና፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማውን ለመፈጸምም በሥልጣን ዘመኑ የመጀመሪያ ተግባሩ ይህንን ግዙፍ የጀግኖች ስብስብ ኢትዮጵያዊ ጦር መበተን ነበር፤ ይህንም አደረገው፡፡ ከኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና እና ታሪክ ባፈነገጠ መልኩ ይህ ታላቅ አስደማሚ የሀገር ታሪክ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ እንኳን እንዳይካተት አደረገ፡፡ የአሸባሪው ትህነግ የሀገር ታሪክ የማጥፋት፣ሀገር የመዝረፍ፣ሀገር የመሸጥ ሴራና የባንዳነት ተግባርም ጊዜው ሲደርስ ተጋልጦ አሁን ላይ ኢትዮጵያያን በአንድነት ዘምተውበታል፡፡ ዛሬ ከጫፍ ጫፍ የተነሳው ኢትዮጵያዊ ለዓመታት በጦርና በገንዘብ ሲዘጋጅና ሥልት ሲነድፍ ቆይቶ ክደት የፈጸመውን ሽብርተኛውን የትህነግ ኀይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ተነስቷል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ከተነሳ ጠላቱን ድባቅ መምታት ልማዱ ነውና፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያዊ እንደ ሽብርተኛው ትህነግ ዓይነት ባንዳ፣ በሃይማኖት እና በእርዳታ ሥም ለሚመጡ አስመሳዮች ቦታ የለውም፡፡ ለዛም ነው ኢትዮጵያዊያን በቁጭት የአያቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እየተቀላቀሉ የሚገኙት፡፡ ኢትዮጵያዊ ምንግዜም ጀግና ነው ሲባል አፈ ታሪክ አይደለም፤ እነዚህ እና እጅግ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ በሚዛናችን ልክ መሆን ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን!
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation