
ሕዳር 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በውስጥና በውጭ፤ በሩቅና በቅርብ ጠላቶች ትብብር የተከፈተብንን ጦርነት ለመመከት እና ሀገራችን የገጠማትን ህልውና የሚፈታተን አደጋ ለመቀልበስ እንደ ሀገር የክተት ጥሪ መተላለፉ ይታወቃል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የክተት ጥሪ እስከ ጦር ግንባር ተገኝቶ ጦሩን በቀጥታ የመምራት ቁርጠኝነት ዋነኛው ግብ ሀገርን ማዳን ነው፡፡ ሀገር ለማዳን ሲባል የማይከፈል መስዋእትነት የለም፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይሎች፣ የሚሊሻ አባላት፣ ፋኖዎችና የፖለቲካ አመራሮች፣ ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና የተለያየ ሙያ ባለቤቶች በግንባር ተሰልፈው መስዋእትነት እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የከበረ የመስዋእትነት መድረክ ላይ በቀጥታ ተሳትፎ ሀገርን ከሽብርተኞች መጠበቅ ታላቅ መታደል ነው፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጥሪም በመስዋእትነት የተጀመረውን ሀገር የማዳን ፍትሐዊ ትግል ወደላቀ ደረጃ እናድርሰውና ኢትዮጵያን አሸናፊ በማድረግ ለዓለም ሕዝብም ሆነ ለመላው አፍሪካ ዳግማዊ ዓድዋን እናብስር የሚል ነው፡፡
ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብም የክተት ጥሪውን ተቀብሎ በዚህ ከፍ ባለ የሞራል መነሳሳት ከቷል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ለሀገሩ ህልውና የከተተ ሕዝብ የተሰማራበት የዘመቻ አይነት ግን እንደየግንባሩ ባህሪ ይለያያል።
ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የክተት ጥሪውን ተቀላቅሏል ካልን የትና እንዴት ዘመተ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የምንዘምተው በተለያዩ ግንባሮች ነው፡፡ ግንባሮቹ ደግሞ በርከት ያሉ ናቸው፡፡ መተኪያ የሌላት እናት ኢትዮጵያችንን የምንወዳት ከሆነ ከሚከተሉት ግንባሮች በምንችለው ቢያንስ በአንዱ ግንባር መዝመታችንን እናረጋግጥ።
• በጦር ግንባር
• በቅርብ ደጀን ግንባር
• በሃብት ማሰባሰብ ግንባር
• በስንቅ ዝግጅትና አቅርቦት ግንባር
• በመረጃና ኮምዩኒኬሽን ግንባር
• በአካባቢ ሰላምና ደህንነት ጥበቃ
ግንባር
• በዘማች ቤተሰቦች እንክብካቤ ግንባር
• በተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ግንባር
• በዲፕሎማሲ ግንባር
• በልማትና መልካም አስተዳደር ግንባር