
ሕዳር 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በግንባር ተገኝተው ጦርነቱን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎ የወገን ጦር ታላላቅ ድሎችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ ገልጸዋል።
በመንግሥት በኩል ወደተሟላ ማጥቃት መገባቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚህም ምክንያት አሸባሪ ኃይሉ የወገን ጦርን የማጥቃት ክንድ መቋቋም እንዳቃተው ጠቅሰዋል፡፡ ጠላት በሚሸሽበት ወቅት ዘርፎና አውድሞ እንደሚፈረጥጥ መታየቱን በመጥቀስ በግንባርና በተወረሩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች መተግበር አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮችንም አመላክተዋል፡፡
1ኛ. አሸባሪው ኃይል አውድሞ እንዳይሄድ በየአካባቢው ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ እና ነቅቶ እንዲጠብቅ
2ኛ. የሚፈረጥጠው የጠላት ኃይል እንዳያመልጥ ታጥቆና ተደራጅቶ እጅ እንዲሰጥ እንዲያደርግ እምቢ ካለም እርምጃ እንዲወስድ
3ኛ. ጠላት በምንም አይነት መንገድ ዘርፎ እንዳይሄድ ለጸጥታ ኃይሎች መረጃ እንዲሰጥ
4ኛ. በሁሉም የደጀን ሥራዎች ላይ ሕዝቡ ተደራጅቶ የወገንን ጦር እንዲያግዝ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው