“ራሱን ለሀገሩ አሳልፎ ለሰጠው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አብሮ በመዝመት እና በመደገፍ ደጀንነታችንን እናረጋግጣለን” የደባርቅ ከተማ ነጋዴዎች

95
ደባርቅ፡ ሕዳር 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጠላትን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላሰለሰ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የደባርቅ ከተማ ነጋዴዎች ተናግረዋል።
ነጋዴዎቹ በተለይ ለአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን እንደተናገሩት እስከ ግንባር ለመዝመትም ዝግጁዎች ናቸው።
አቶ ባዘዘው አዛኔ የተባሉ ነጋዴ አኹን በሰላም እየነገድኩ ያለኹት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመኖሩ ነው ብለዋል። ቁርና ሃሩር ሳይበግረው ጠላትን በጀግንነት ለሚፋለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት።
ባንዳነቱን በገሀድ ያስመሰከረው አሸባሪው የትግራይ ወረራ ኀይልን እየደመሰሰ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ኹሉ ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሙሉዓለም አማኔ የተባሉ ነጋዴ ናቸው። ድጋፍ መስጠት ብቻ ሳይኾን ለመዝመት ዝግጁ እንደኾኑም ተናግረዋል።
አቶ ፋሲል ውቤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወራሪውን ኀይል በመደምሰስ አኩሪ ጀብድ እየፈጸመ ነው ብለዋል። በጠላት ወረራ ምክንያት የተፈናቀለው ማኅበረሰብ ወደ ስፍራው ሊመለስ የቻለው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ተጋድሎ እንደኾነም ገልጸዋል። በወቅቱ ከወገን ሠራዊት ጋር በመኾን ታግለው እንደነበረም አስታውሰዋል። “እንደ ወትሮው ኹሉ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የምናደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ያሉት ነጋዴው ለመዝመትም ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ሀገርን ለማፍረስ ቢፍጨረጨርም የሀገር መከላከያ ሠራዊት አከርካሪውን ሰብሮታል፤ እየሰበረውም ይገኛል ያሉት ደግሞ አቶ ማንደፍሮ ፈንታ ናቸው። በተደጋጋሚ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ማድረጋቸውን የጠቆሙት አቶ ማንደፍሮ ወደ ፊትም ከድጋፍ በዘለለ ወደ ግንባር ዘምተው ጠላትን ለመፋለም ቁርጠኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:-ቡሩክ ተሾመ-ከደባርቅ
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
Previous articleየኪነ ጥበብ ባለሙያዎች “ተከትለንሃል” በሚል ወደ ጦር ግንባር እየዘመቱ ነው።
Next articleበአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ መንግሥት አስታወቀ፡፡