
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግንነት እንደ ዥረት የሚፈስባት፣ ጀግኖች እንደ ቡቃያ የሚበቅሉባት፣ ጠቢባን የሚፈልቁባት፣ ሊቃውንት የተፈጠሩባት፣ የሚፈጠሩባት፣ የሚኖሩባት፣ እልፍ ታሪኮች ያደመቋት፣ እልፍ ጀብዱዎች ከፍ ያደረጓት፣ በታሪኳ ውስጥ ከማሸነፍ በስተቀር መሸነፍ ያልተገኘባት፣ ጠላት የሚቀጣበት፣ ባዕድና ባንዳ የማይደፍራት፣ ቀዳማዊት፣ ምስጢራዊት የሆነች ሀገር። ምድሯ በረከት ያለበት፣ ረቂቅነቷ ተመርምሮ ያልተደረሰበት፣ የጀግና ልጆቿ ገድል አቻ ያልተገኘለት ውብ ሀገር ኢትዮጵያ።
ልጆቿ ይኮሩባታል፤ ኮርተውም ያኮሯታል፤ ተስፋም ያደርጉባታል። ጠላቶች ይቀኑባታል፤ የክፋት እጃቸውን ያነሱባታል፤ በክፋት ዓይናቸውም ያይዋታል፤ እርሷ ግን ጀግና መውለድ ታውቃለችና በክፉ የሚያይዋትን ታጠፋቸዋለች፤ በክፉ የሚነሱባትን ትደመስሳቸዋለች። ለነዚህ ምሕረት የላትም። ከኢትዮጵያውያን በላይ ጀግና የሚፈጠር አይመስልም። እነርሱ በየዘመናቱ ተፈትነው አሸንፈዋል፤ የመከራውን ዘመን በድል አልፈዋል፤ የበደለኞችን አብዮት አንኮታኩተዋል፤ የነጭን የበላይነት ዘመን ቋጭተዋል፤ እኩልነትን በዓለም ላይ ዘርተዋል፤ የነጭን አንገት አስደፍተዋል፤ የጥቁርን አንገት አቅንተዋል። ሁሉም ይገረምባታል፤ አጀብ ሲልም ያደንቃታል፤ ኢትዮጵያን።
ኢትዮጵያ በጀግንነት የፀናች፣ ለማንም ያልተበገረች ሀገር ናት። ልጆቿ ለኢትዮጵያ መሞት፣ ለኢትዮጵያ ሁሉን መስጠት ሰማዕትነት፣ በረከት፣ መመረጥ፣ ከሁሉም መብለጥ ነው ይላሉ። ለምን ካሉ እርሷ ከምንም በላይ ናትና። ኢትዮጵያ በጥበብ የተጠበቀች፣ በረቂቅ ትሩፋቶች የተሞላች፣ በአሸናፊነት የፀናች፣ ጥበባትን፣ ምስጢራትን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ ቅዱሳት መካናትን ታቅፋ የኖረች፣ ታቅፋ ያለች ሀገር ናት። እርሷ እንዳደረገችው ያደረገ የለም፤ እርሷ እንዳላት ያለው የለም፤ ከሰማይ የተላኩ የምድር በረከቶች ሁሉ በእርሷ ላይ አሉ። ከእርሷ ጋር ይኖራሉ። ለሰዓታት ሳይጓደል የፈጣሪ ስም የሚጠራባት፣ የሰማይ በረከትና ረድኤት የሚለመንባት፣ በየቀኑ በረከት የሚሰጣት ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ።
በየፈርጁ የማያንቀላፉ ወታደሮች አሏት። ምድራዊ የሆኑ ጠላቶቿን በጦር በጎራዴ የሚወጉላት፤ በተራራና በሸንተረሩ ጠላቶቿን የሚደመስሱላት፤ የሚቀጡላት፤ መንፈሳዊ የሆኑት በቅዱስ መንፈስ እርኩስ መንፈስን የሚያርቁላት። ሁለቱም አያንቀላፉም። ትጉሆች ናቸውና የፈለጉትን ያገኛሉ፤ ያቀዱትን ያሳካሉ፤ ሀገራቸውን ያስከብራሉ። ጥቁር መመኪያና ተስፋ እንዲያጣ፣ የኢትዮጵያ ኃያል ታሪክ ከታሪክ ድርሳን ላይ እንዲታጣ ጠላቶች ያላደረጉት የላቸውም። ዘመን ዘመን እየተካ በሄደ ቁጥር ጠላቶችም የክፋት እጃቸውን እያነሱ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። ታሪኳን ሊያጠለሹ፤ የነፃነት ብርሃንነቷን ሊያጠፉ ጦር አዝምተዋል፤ በውሸት ትርክት ገብተዋል፤ ለመከፋፈል ሞክረዋል። አንደኛውም እቅድ አልሰመረላቸውም።
ሁሉም የክፋት እቅዶቻቸው ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያውያን ልዕልና በታች ነውና ተሽንፈው ይመለሳሉ። ዳሩ ጠላቶቿ አርፈው አይተኙም። አባቱ ያላገኘውን እድል ልጁ አገኘዋለሁ በሚል የሞኝ ተስፋ ይነሳል። እርሱም የኢትዮጵያውያንን አጅ ይቀምሳል። አፍሮ ይመለሳል። ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ ነው የኖረችው። እንደ ዛሬው ታንክ ሳይጫን፣ ብሬን ሳይደረደር፣ የአየር ድብደባ ሳይኖር ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በጋሻ እየመከቱ፣ በሰይፍ እየሸለቱ፣ በጦር እየወጉ ጠላትን ደምስሰዋል። ሀገራቸውንም አስከብረዋል። አያሌ ዘመናትን በፈረስ ሸምጥ ጋልበው፣ በባዶ እግር ተራምደው ጠላታቸውን ቀጥተዋል።
ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ፈረሶችም ውጊያ አዋቂዎች ናቸው። እየሰገሩ እየሄዱ ከጠላት ሩጫ እየቀደሙ ለጌታቸው ግዳዩን ያመቻቻሉና ፈረሶችም ለጀብዱዎች ታላቅ ድርሻ ነበራቸው። የቀደሙት ፈረሰኛና እልኸኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሀገር ስትደፈር፣ ጠላት ወሰኑን ሲሻገር እምብኝ ብለው ተነስተው ነብሱን አስተው መልሰውታል። ሆኖለት የሚያሸንፋቸው፣ ጀግኖ የሚረታቸው ጠላት እስካሁን በምድር አልተፈጠረም። ወደፊትም አይፈጠርም። እነርሱ ለአሸናፊነት ብቻ የተፈጠሩ ናቸውና አሸናፊነትን ከእነርሱ የሚወስድ የለም። ጀግንነትን የሚነጥቅ አይገኝም። ዛሬማ ያ ዘመን አልፎ ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቀው ማን ሊረታቸው? ማንስ ሊገፋቸው?
በኢትዮጵያ ውትድርና ሕይወት ነው። ኑሮም ነው። በአንድ ወቅት አራሽ የነበረው ገበሬ ኢትዮጵያ ተነካች ተብሎ ሲሰማ ተኳሽ ወታደር ሆኖ ይመጣል። ሞፈርና ቀንበሩን ጥሎ፣ ሳንጃውን ስሎ፣ ጠመንጃውን ወልውሎ ጠላት ወደ መጣበት፣ ጀግንነት ወዳለበት፣ ጀብዱ ወደሚሠራበት ይጓዛል። ይህን ዛሬም እየታየ ነው ያለው። ገበሬዎች ወታደሮች ሆነው ዘመቻ ገብተዋልና። ድሮ ቀለብ ያልተሰፈረላቸው፣ ስንቅ ያልተጫነላቸው፣ ደሞዝ ያልተቆረጠላቸው፣ ጥይት ያልተገዛላቸው፣ ሁሉ በራሳቸው ትጥቅ በራሳቸው ስንቅ እየዘመቱ፣ ሀገር ነፃ አውጥተዋል። የእነዚያ ጀግኖች፣ አርበኞች ልጆች ዛሬም ለእናት ሀገራቸው እንቅልፍ አጥተዋል፤ ከራስ በላይ ሀገር በሚለው መርሃቸው መክረሚያቸውን ምሽግ አድርገዋል። የአባቶቻቸው ልጆች ጀግና ወታደሮች።
የኢትዮጵያ ወታደር ልቡ የሞላ፣ መውጊያው የማይላላ ጀግና ነው። በርካታ መሰናክሎች ከፊቱ ቢደረደሩም፣ የማይታለፉ ተራራዎች ያሉ ቢመስሉም ሁሉንም በፅናት እና በጀግንነት ያልፋቸዋል፤ አልፏቸዋል። የሰማይ መብረቆች፣ የምድር እሳቶች የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የተነሳውን አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ኃይል ለማጥፋት እየደቆሱት ነው። በሰማይም በምድርም እየወረዱበት ነው። በሰማይ በአየር፣ በምድር በእግር እየሰገሩ መውጫ መግቢያ አሳጥተውታል። የተገፋው፣ የተካደው፣ በጀርባው የተዋጋው ጀግናው የኢትዮጵያ ወታደር የካደውንና ከጀርባው የወጋውን ጠላት በሳምንታት ልዩነት ፍርክስክሱን አውጥቶ ብዙን ገድሎታል። ተስፋ የቆረጠው ከሃዲ ኃይልም ከተበተነበት ጉድጓድ ተሰባስቦ ዳግም ሀገር ወረራ ላይ ነው። ጀግናው ወታደርም ሀገርና ሕዝብን ለመታደግ ጠላትን ድባቅ እየመታው ነው። ከራሱ በላይ ሀገሩን አስቀድሞ፣ ኢትዮጵያ የምትለውን ስም አንግቦ እየደመሰሰው ነው።
የኢትዮጵያ ወታደር ጀግና ነው፤ ፍርሃት ያልፈጠረበት አንበሳ ነው፤ ጠላትን አድቃቂነቱ የተመሰከረለት፣ በሠንደቁ ቃል ኪዳን አስሮ፣ እንደ ነበር ተወርውሮ፣ ጠላትን ሰብሮ ይጥለዋል። <<ኢትዮጵያ እናቴ የወለደችው፣ አይፈራም እሳ ምን አበላችው>> የሚባልለት፡፡ ተራራዎች የማይበግሩት፣ ዋሻዎች የማይቀሩት፣ የበረሃው ንዳድ የማያደክመው፣ የደጋው ቆፈን ከእርምጃው የማይገታው ጀግና የጀግና ልጅ ነው። ይህን ወታደር አለማድነቅ አይቻልም። በጎዳናዎች ሲያልፍ ቆሞ ሊጨበጨብለት፣ ስሙ በተደጋጋሚ ሊጠራለት የሚገባ የተከበረ፣ የጠላትን ምሽግ የሰባበረ፣ የጠላትን ምኞት ከንቱ ያስቀረ፣ ሀገሩን ያስከበረ ነውና የጀግንነቱ ልክ ወሰን ያጣል።
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጠላታቸውን እየደመሰሱ፣ ጋራና ሸንተረሩን እያሰሱ ግስጋሴ ላይ ናቸው። አንተም አድንቃቸው፤ አይዟችሁ በላቸው፤ ጉሮሮአቸውን ያርሱበት ውኃ፣ ረሃባቸውን ያስታግሱበት ምግብ አቅርብላቸው። መንገድ ምራቸው፤ የተሸከሙትን ተቀብለህ ሸኛቸው፤ አቀበቱን አውጣቸው፤ ቆልቁለቱን አውርዳቸው። እነርሱ ሀገርን የሚያክል አደራ በልባቸው፣ ትጥቅና ስንቅ በጀርባቸው ተሸክመው ለዓመታት እንደሚጓዙ አስብ። አደራቸውን ካልተወጡ፣ ጠላትን ቀጥቅጠው ሰላም ካላመጡ በስተቀር የተሸከሙት ስንቅ አይወርድም። ስንቅ ስታቀርብላቸው እነርሱ ለዘመናት በዚህ ሕይወት ውስጥ እንደሚኖሩ አትርሳ።
አንተ እንድትተኛ እነርሱ በድንበር ቆመዋል፤ አንተ ጮማ እንድትጎርስ እነርሱ ደረቅ እየበሉ፣ የኮዳ ውኃ እየተካፈሉ ነው። ወታደሩን ካላከበርክ ከክብርህ ትወርዳለህ፤ የምትመካባትን ሀገር ታጣለህ፤ በጠላት ትወረራለህ። ለእነርሱ ሳይሆን ለሀገርህና ለክብርህ ስትል አክብራቸው። ደግፋቸው፣ አለሁ በላቸው። አሁን በኢትዮጵያ ላይ የተነሳውን ጠላት እንደ ገብስ እያጨዱት፣ በገባበት ሁሉ እየደመሰሱት፣ መውጫም መግቢያም ነፍገውት ተጨንቋል። አብዛኛው አልቋል። የቀረው ተደናብሯል። ጀግኖቹም የተደናበረውን፣ ተደናብሮ ቀዬ ለማርከስ የገባውን እያደኑ እየለቀሙት ነው።
የምትናፍቀው ሰላም በቶሎ እንዲመጣ ከፈለክ ከጀግኖች ጋር አብር፤ ከእነርሱ ጋር ኑር። ትንሽ ነገር ከሰጠሃቸው ትልቋን ሀገርህን ከነክብሯ ያቆዩልሃል፤ የምትሻውን ሰላም ይሰጡሃል። የሰማይ መብረቆቹ ነጎድጓዳቸው በዝቷል፤ ግዳያቸውም በርክቷል። የነጎድጓዳቸው ብዛት ጠላትን እያበራየው ነው። አንድ ነገር እመን ማሸነፍ የተፈጠሩበት፣ ያደጉበት የኖሩበት ነውና በቅርብ ሁሉንም አሸንፈው በኢትዮጵያ የሰላም ፀሐይ እንደሚያበሩ።
አንድ ነገርም ልብ በል ከፊትህ እኛ አለን ከኋላችን አትለዬን ደጀን ሁነን የሚሉትን አትርሳ። የሚጠበቅብህን አድርገህ የሚጠበቅባቸውን ብትጠይቃቸው ሳያጓድሉ ይመልሱልሃል። አድርጉ ብትላቸው አንድም ሳያስቀሩ ያደርጉልሃል። ክብር ይገባቸዋልና፤ ክብር ለእነርሱ ወጥተው ለሚያድሩት፤ ወጥተው ለሚኖሩት ለወታደሮች ይሁን።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
