የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለህልውና ዘመቻው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡

438
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጫ ሠጥቷል፡፡ መግለጫውን የሠጡት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ መሐመድ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል በወረራቸው አካባቢዎች በርካታ ጥፋቶችን እያደረሰ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሼህ ሰይድ እንዳሉት ይኽን ወራሪ ኀይል መደምሰስ ለአንድ አካል ብቻ የተተወ መሆን የለበትም፤ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል፤ በዚህም የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በአንድ ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ወስነዋል፡፡
ምክር ቤቱ ካሁን ቀደም ለመከላከያ ሠራዊት እና ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብ እና የቁሳቁስም ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ነው የገለጹት፤ ፕሬዚዳንቱ ሁሉን አቀፍ ድጋፉ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጋር በመቀናጀት በክልሉ ከሚገኙ በሁሉም መስጅዶች ገንዘብ በማሰባሰብ የሠላም ሚኒስቴር በከፈተው የባንክ ሒሳብ ቁጥር ገቢ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በጋራም ሆነ በተናጠል እያደረገ ያለው ድጋፍ ይበል የሚያሠኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሁሉም ሀገር ወዳድ ለዘመቻው በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ ጸሎት እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleቤታቸውን ሸጠው ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ገንዘብ የለገሱ እናት…
Next articleአርቲስት ታማኝ በየነን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦች እና የቀድሞ ጦር ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ግንባር ዘመቱ።