
ሕዳር 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የታሪክ መምህርና የሀገር ሽማግሌ ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕወሓት የሽብር ኃይል ጋርና ሉዓላዊነቷን ከተዳፈሩት አንዳንድ ምዕራባውያን ጋር የገባችበትን ጦርነት አስመልክቶ ለጥቁር የአፍሪካ ሕዝቦች ያስተላለፉት ጥሪ ተቀዛቅዞ የነበረው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዳግም እንዲጀምር ከማድረግ አንፃር የራሱ የሆነ በጎ ተጽዕኖ አለው፡፡
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 1960ዎቹ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መውጣት የመሠረት ድንጋይ የጣለችና በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት በኩል ስለ አፍሪካ ብዙ የተሟገተች ሀገር ስትሆን በዚህም በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች የነፃነት ተምሳሌትና እናት አድርገው እንደሚመለከቷት አውስተዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጥሪ አንዳንድ ምዕራባውያን ዳግም እያመጡብን ያለውን የባርነት ቀንበር በጋራ እንስበር ከሚል የመነጨ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች በመልካም እየተቀበሉትና በጎ ምላሽ እየሰጡት መሆኑን ሰሞኑን እየታየ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹በተለያዩ አገራት የሚገኙ አካላት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት ብቻዋን እየተዋጋች ነው ከሚል ንግግር አንስቶ የ “ይበቃል” መፈክርን በመያዝ የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እስከማስተጋባት ደርሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት የአፍሪካውያንም ነው የሚል እሳቤ እየተፈጠረ ነው›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ፤ ይህ ደግሞ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ምን ያህል እየተመለሰ እንደሆነ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ አንዳንድ ምዕራባውያን በአፍሪካ ተባብረን እንደግ የሚል መንግሥት ሲነሳ የማፈንና ከሥልጣን እንዲወገድ የማድረግ ልምድ ያላቸው ሲሆን፤ ዶክተር ዐቢይ ደግሞ አፍሪካን ያማከለ የመልማት ሐሳብ ይዘው ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ጥርስ ውስጥ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት ጥሪ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ዳግም በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ የተነሳሱ ሲሆን ይህንን አስፍቶ ሁሉም ዘመቻውን እንዲቀላቀል ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የውስጥ ችግር ቢወጠሩ ሉዓላዊነታቸውን የሚገዳደር ጠላት ሲመጣ “ኢትዮጵያ” የሚል አንድ ቃል ተናጋሪ ናቸው፡፡ ተመልከት ዓላማህን! ተከተል አለቃህን! በሚለው ብሂል መሠረት መቆየታቸውን ታሪክ ያረጋግጣል የሚሉት መምህሩ፤ አሁንም ቢሆን አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እየቀለቡትና እየነዱት የመጣውን የሽብር ኃይል በጋራ የመመከት አቅም አላቸው ነው ያሉት፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
