
የክልሉ ሕዝብ በመሰል ችግሮች ውስጥ እንዳያልፍ ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ አስተያዬት ሰጪዎች ተናገሩ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰሞኑን በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ አስተያዬት የሰጡ የምስራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ድርጊቱ አሳዛኝ የሴረኞች ኢላማ ነው፤ መንግሥት ከግጭቶች ሕዝብን ለመታደግ ኃላፊነት ወስዶ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተፈፀመው ግጭት በክልሉ የሚገኙ ሕዝቦችን ለማጋጨት የታለመ የማይሳካላቸው ፖለቲከኞች ርካሽ ተግባር ነው ብለዋል አስተያዬት ሰጪዎቹ፡፡ የአማራ ክልል በሚፈጠሩ ሴራዎች የሚከሰቱ ችግሮችን በመፍታት ብቻ እንዲጠመድ ከሚያዘናጉ ልዩነት አጥማቂ ማኅበርተኞች ሕዝቡ ተጠብቆና ቀድሞ በመንቃት ችግሮችን ከክልሉ መንግሥት ጋር በመቆም ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንደሚገባም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንግሥትም በግለሰቦች የአሠራር ብልሹነት ምክንያት ሕዝባዊ ጥቅሞች እንዳይዳፈኑ በመገምገም መፍታትን ቀዳሚ ማድረግ እንዳለበት አስተያዬት ሰጪዎች አመላክተዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር በንፁሃን ዜጎች እና በልዩ ኃይሎች ላይ የደረሰው ሞት አሳዛኝ ነው፤ አጥፊዎችን የክልሉ የፀጥታ ኃይል እና የፌዴራል ደኅንነት አስቀድሞ መከላከል ይኖርባቸዋል፤ አስቀድሞ መከላከል ካልተቻለ ለዜጎች ሕይወት መጥፋት እና ክልሉንም ከልማት ይልቅ በኪሳራ ጥገናዎች ላይ እንዲያሳልፍ የሚያደርጉ ክፍተቶች ናቸው ብለዋል፡፡
አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን የአማራ ክልል በቀውስ ውስጥ እንዲያሳልፍ ለማድረግ ጉዳዩን ሳይረዱ የማሸበር ሥራ እየሠሩ ነው፤ ጉዳዩንም ሕዝባዊ ፀብ ለማስመሰል የሄዱበት ርቀት ትክከል አይደለም ብለዋል ነዋሪዎቹ። መንግሥት ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ ስለ ችግሩ ከመናገር ይልቅ አስቀድሞ ችግሩን መከላከል እንደሚገባውም አስተያዬት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡
“ዋጋ ያስከፈለን ግቡ የማይሳካ የፖለቲካ ልምሻ ነው” ያሉት ነዋሪዎቹ የክልሉ ሕዝብ ከዚህ በኋላ በመሰል ችግሮች ውስጥ እንዳያልፍ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ የልዩነት ሀሳቦችን መድረክ በመፍጠር መፍታትና ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከል እንዳለበትም ጠይቀዋል፡፡
ችግሩ እንዳይደገም የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ግጭቶችን ቀድመው መከላከል እና የመፍትሔ ሀሳብ መተግበር እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።
ከምዕራብ ጎንደር ዞን ባሻገር በክልሉ የግጭት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ የሴረኞች የግጭት መፍጠሪያ አከባቢዎች ላይ በትኩረት መሥራት፤ ግጭቶችን የፈጠሩ ኃይሎች ላይም ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ዘላቂ የሰላም ቀጣና እንዲሆን ከሁሉም አካላት ጋር በመግባባት በንቃት መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- ግርማ ተጫነ