
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) (አሚኮ) የታሪክ መጽሐፊያ ብዕር፣ የታላቅ ሀገር የጋራ ዜማ መዝሙር፣ የጀግንነት መነሻ፣ የኃያልነት መዳራሻ፣ የመከራ ቀን ማለፊያ፣ የማዕበል ዘመን መቅዘፊያ፣ የሁልጊዜ መኩሪያ፣ የጨለማ ቀን መውጫ መንገድ፣ የታላቅ ሕዝብ ማስተሳሰሪያ ገመድ፤ ከሰንደቅ በፊት ይዋደቃል።
እናት ሀገሩን ልድፈር ወደ አለው ሳንጃ ስቦ ጦር ይሰብቃል። መነሻው የሀገር ፍቅር፣ መዳረሻው የሀገር ክብር፣ ደልቶት አይኖርም፣ ተዝናንቶ አያድርም፣ ማደሪያው ምድር ቆፍሮ፣ ምግቡ ኮቸሮ፣ ለሕይወቱ አይሳሳም፣ ውድ ሀገሩን አያስነካም ጀግናው ወታደር።
ወታደር ታሪክ በደም የሚፃፍበት ብእር፣ ኮርተው የሚናገሩለት ዝና፣ ከዘመን ዘመን የሚዜምበት ዜማ ነው። ጀግንነት በሚበዛበት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደመቅ ያለው የወታደር ነው። ጦረኛ ኢትዮጵያዊ ባይኖር፣ የማያወላውል ጀግና በምድሯ ባይፈጠር ዓድዋ ተራራ እንጂ ድል ባልሆነ ነበር። የአፍሪካ ምድር በጨለማ በኖረ ነበር። ኢትዮጵያን እንገዛለን፣ ኢትዮጵያውያንን እናስገብራለን፣ ኢትዮጵያዊነትን እናጠፋለን ያሉት ሁሉ በጀግና ልጆቿ ጠፍተዋል።

የኢትዮጵያውያን ቁጣ መብረቅ ነው፤ አድርቆ የሚጥል፣ ምትሃት ነው፤ ከሥሩ የሚነቅል፣ ረቂቅ መንፈስ ነው፤ ነብስን ከሥጋ የሚነጥል፣ በዘመናት ቅብብል ኢትዮጵያን አጠፋለሁ ያለ የጠላት ማዕበል በወታደር ተመልሷል፣ ለኢትዮጵያውያን ይሁን የተባለ የክፋት ፅዋ ከድንበር ማዶ ፈስሷል። የተቆለለ የጠላት ገደል ፈራርሷል። ትዕቢት የገፋው ጠላት ሁሉ የኢትዮጵያውያንን ክንድ ቀምሷል።
ኢትዮጵያዊነት ማሸነፊያ፣ ኢትዮጵያዊነት የጨለማን ዘመን ማለፊያ፣ ኢትዮጵያዊነት ኩራት፣ ኢትዮጵያዊነት ፅናት፣ ኢትዮጵያዊነት ቀዳሚነት፣ ኢትዮጵያዊነት አይለወጤነት፣ ኢትዮጵያዊነት የድል ምልክት፣ ኢትዮጵያዊነት የመልካም ነገር ተምሳሌት ነውና። ከኢትዮጵያዊነት ላይ ውትድርና ሲጨመርበት ደግሞ ግርማው ልዩ ነው። የዓድዋ የድል ጥላ፣ የአምስት ዓመቱ የአርበኝነት መላ፣ ጠላት የማይፈታው ቀመር፣ የማይመረምረው ምስጢር፣ ኢትዮጵያዊ የማያወልቀው ዘላለማዊ ክብር ነው።
ኢትዮጵያዊያን በራስ ትጥቅና ስንቅ እየዘመቱ ማንነት እስከነ ክብሩ፣ ሀገር እስከ ድንበሩ አቆይተዋል። የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ሲያልፉም የማይሻር፣ የማይረሳ ቃል ኪዳን አደራ ብለዋል፣ ልጆቻቸውን በቃል ኪዳን አስረዋል። ቃል ኪዳን ያሰራቸው፣ የአባቶቻቸው የጀግንነት ታሪክ ያላስተኛቸው፣ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር የዋጃቸው፣ የሀገር ክብር የጠራቸው ጀግና ልጆች ዛሬም እንደ ትናንቱ “እማማ ሆይ አለንልሽ፣ እኛ እያለን ክብርሽም ስምሽም ዝቅ አይልም” እያሉ ነው።
“አልማከርም ከፈሪ ጋራ፣
ያስደፍረኛል ወሬ ሲያወራ” የሚሉት ጀግኖቹ ምክራቸው ከጀግና ጋር ውሏቸው ከሀገር ድንበር ነው።

ድሎት ሳያምራቸው፣ የወገን ናፍቆት ወደኋላ ሳይጎትታቸው፣ መከራ ሳያደክማቸው፣ ቁሩና ሀሩሩ ሳይበግራቸው፣ ለእማማ ኢትዮጵያ ምቾትንና ሕይወትን ሰጥተው ይኖራሉ። ስለ እርሷ ሲሉ ይኖራሉ፣ ስለ እርሷም ያልፋሉ። በስሟ ምለው፣ ለቃሏ ታምነው፣ ለክብር ብለው መሪር ፅዋን ይቀምሳሉ፣ ክፉ ቀንን ይታገሳሉ።
“እኔ ላገሬ አደራ አለብኝ፣
ጎጆ ትዳሩም ከዚያው ይቅርብኝ፣
ሀገሬን ጠላት ከሚደፍርብኝ፣
ድንበር ዘምቸ ከሠንደቋ ሥር መሞት አለብኝ” እንዳለ አርበኛው ሁሉም ነገር ይቅርብኝ ብለው ለሀገር ማገር፣ ለወገን ክብር ሊሆኑ ፅኑ ቃል ኪዳን አስረዋል።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
