
ደባርቅ፡ ሕዳር 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በደባርቅና ዳባት ወረዳዎች ወረራ የፈፀመውን አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይል የሰሜን ጎንደር ሕዝብ ከወገን ጦር ጋር በመቀናጀት መደምሰሱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ወቅት ታላቅ ተጋድሎ የፈፀሙት የዳባት ወረዳ ወጣቶች ለሕይወቱ የማይሳሳ ጀግና መከላከያ ሠራዊት እንዳላቸው በግንባር ተመልክተዋል፡፡
የዳባት ከተማ ነዋሪ ወጣት ገብረሕይወት ፈንቴ በሰሜን ጎንደር በተካሄዱ ውጊያዎች መሳተፉን ተናግሯል፡፡ በጭና ቀበሌ በተደረገው ውጊያ ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጋር ተቀንጅቶ በመዋጋት ከወራሪው ኀይል ብሬን እንደማረከም ነው የተናገረው፡፡ ወጣት ገብረሕይወት በታገለባቸው አውደ ውጊያዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን ጀግንነት በዓይኔ ተመልክቼ አረጋግጫለሁም ብሏል፡፡
የዳባት ከተማ ነዋሪ ሃምሳ አለቃ ክንዱ ገበየሁ በበኩላቸው ‟በደባርቅና ዳባት ወረዳዎች በተደረጉ ውጊያዎች ለሕይወቱ የማይሳሳ ጀግና የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዳለን አብረን ታግለን አረጋግጠናል” ነው ያሉት፡፡ሃምሳ አለቃ ክንዱ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ጀግንነት ለመግለጽ ቃላት የለኝም ነው ያሉን፡፡ የሰሜን ጎንደር ሕዝብም ሠራዊቱን በመደገፍና አብሮ በመወጋት ተጋድሎ የፈፀመ ሕዝብ ነውም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጀግኖች አባቶችን ታሪክ ለመድገም ወደ ግንባር መዝመታቸው በዳባት ሕዝብ ላይ መነቃቃትን መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡ የሀገሪቱ መሪ ወደ ግንባር ሲዘምቱ ሀገሪቱ ያጋጠማትን ፈተና በግልፅ የሚያሳይ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተከትለው የመከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ወደግንባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለአሚኮ እንዳረጋገጡት ጀግና የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መቀላቀል መታደል ነው፤ በመሆኑም ይህን እድል መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡-አድኖ ማርቆስ-ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
