
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአሁኑ ወቅት በተለይ ምዕራባውያን ሀገራት ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በኩል እንዲፈጸምላቸው በመፈለግ ብዙኃን መገናኛ ተቋሞቻቸው ጭምር የሐሰት መረጃ በማሰራጨት ተጠምደዋል።
አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያኑ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያ የፈጸማቸውን እና አየፈጸማቸው ያሉ የሰብዓዊ ጥሰቶችን እያዩ እንዳላዩ አልፈውታል፡፡
በተቃራኒው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እያደረጉት ያለውን ዘመቻ ለመተቸት እና አቃቂር ለማውጣት የሚቀድማቸው የለም፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጫና ለማሳደር እንቅልፍ አጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ላይ የሚደረግ ይህ ዓይነቱ ጫና እና ደባ በየትኛውም አግባብ ተቀባይነት እንደሌለውና ሉዓላዊነትን መዳፈር እንደሆነ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምሕር መኳንንት ዱቤ ተናግረዋል። በተለይም አንድ ሉዓላዊት ሀገር በውስጥ ባንዳዎች የመደፈር አደጋ ከገጠማት የራሷን አቅም በመጠቀም የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እና ደኅንነት የማስከበር ግዴታ እንዳለባት የዓለም አቀፍ ሕጎችም ጭምር ይደነግጋሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብም ሽብርተኛውን የትግራይ ወራሪ ኃይል ለመደምሰስ አሁን እያካሄዱት ያለው የህልውና ዘመቻ የዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ያደረገና ራስን የመከላከል ዘመቻ መሆኑን የሕግ መምሕሩ አስረድተዋል። እንዲህ ዓይነት ድንጋጌዎች በዓለም አቀፍ የዩኤን ቻርተር፣ በአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያ ሠነድ እና በቬና ኮንቬንሽን ላይ በግልጽ የተቀመጡ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
እናም “የአንድ ሉዓላዊ ሀገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ብሎ የፈረጀውን ቡድን መደገፍ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት መዳፈር ነው” ብለዋል መምሕር መኳንንት።
መምሕሩ እንዳብራሩት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመወሰን ለበርካታ ጊዜ ስብሰባ የተቀመጠው የፀጥታው ምክር ቤት ሳይስማማ የሚበትነውም በሕግ አግባብ ሰለማያስኬድ ነው፤ ይህም ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደርጋታል፡፡
በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀስ የሽብር ቡድንን አድኖ በሕግ ፊት የማቅርብ ኀላፊነት ለሀገሪቱ መንግሥት የተሠጠ እና ግዴታም መሆኑን በዓለም አቀፍ ሕግ ጭምር የተደነገገ መሆኑን መምሕሩ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ሽብርተኛ ቡድኑን አድኖ በሕግ ፊት ማቅረብ ካልተቻለ ደግሞ ተከታታይ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ሥልጣን ያለው መሆኑንም አስገንዝበዋል።
መምሕሩ የዓለም አቀፍ ሕጎች ተፈጻሚ እንዲሆኑና ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዲኖራት ሕዝቡ በጀመረው አግባብ በመደራጀት መከላከያን እና ልዩ ኃይልን መደገፍ እና ለህልውና ዘመቻው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አስተያየት ሠጥተዋል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል የፈጸማቸውን ጭፍጨፋዎች እና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማጋለጥ ጫና እንዲፈጥሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የተማረው ክፍልም አሁን እያደረገ የሚገኘውን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማጠናከር የሽብር ቡድኑ እየፈጸመ የሚገኘውን ግፍ ለዓለም ማኅበረሰብ ማጋለጥ አለበት፤ ሁሉም ሰው ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ በማድረግ ወረራውን በአጭር ጊዜ መቀልበስ እንደሚቻል የሕግ መምሕሩ አስተያየት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
