
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2012 ዓ/ም (አብመድ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ መስሪያ ቤት የ2011 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸሙን ገምግሟል። በግምገማ ሂደቱ ላይ የተሳተፉት የደቡብ ወሎ ዞን ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ መምሪያ የወንጀል የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አብርሃም ሞላ እና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ዐቃቢ ሕግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገሩ ሙሉ እንዳሉት የፖሊስ የምርመራ ጥራት ችግር፣ የክስ ጥራትና ሀሰተኛ ምስክር ለፍትሕ ስርዓቱ ችግር እንደነበሩ አንስተዋል።
በአዲሱ ዓመት በፍትሕ ሥርዓቱ የተሻሻሉ አሠራሮች በመተግበራቸው የተንዛዛ አሠራርን ለማስቀረት እገዛ እንደሚያደርጉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ታች ድረስ ኅብረተሰቡን በማነጋገር ችግሮቹን ለይቶ ለመቅረፍ መሞከር ለችግሩ ወሳኝ መፍትሔ ነው ያሉት የሥራ ኃላፊዎቹ በተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ 263/2011 ላይ እንደተመላከተው በኃላፊነት ደረጃ ጣልቃ ገብነት በእስራትና በገንዘብ የሚያስቀጣ በመሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱ ከጣልቃ ገብነት ወጥቶ ከሚመለከታቸዉ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት እንዳለበት አመልክተዋል። “አቅም በሚችለዉ ሁሉ መሰዋዕትነት ከፍለንም ቢሆን የኅብረተሰቡን የፍትሕ ችግር እንቀርፋለን፤ የሚጠበቅብንንም እንሠራለን” ብለዋል።
አብመድ ያነጋገራቸዉ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ገረመዉ ገብረጻዲቅ ደግሞ በጥራት፣ ፍትሐዊነት በማረጋገጥና ሁሉንም ዜጎች በእኩል በማስተናገድ በኩል በርካታ ችግሮች እንዳሉ አመልክተዋል። “በኅብረተሰቡ በኩል ታማኝነት ያተረፉ የፍትሕ ተቋማትን መገንባት እንዳለብን እናምናለን” ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ “በዚህ ጊዜም በየተቋማትና በኃላፊዎች ሌብነትና ዝርፊያ የተበራከተበት፤ የመንግሥት ሀብት እየባከነ ያለበት፤ ዜጎች በአግባቡ የማይስተናገዱበት፤ የሕግ የበላይነት ያልሰፈነበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነዉ›› ብለዋል።
ጠቅላይ ዐቃቢ ሕጉ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለዉን ችግር በጥልቀት አለመገምገም፣ የሥነ ምግባር፣ የብቃት፣ የተቋማት ጥንካሬና አሰራር አለመፈተሽ እንዲሁም አገልግሎቱ አለመዘመኑ የችግር ምንጮች እንደሆኑም አመላክተዋል፡፡ በየደረጃዉ የሚገኘው የጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ኃላፊና ባለሙያ በተልዕኮው ላይ የጋራ መግባባት እንደሚያስልገው የጠቆሙት አቶ ገረመው ‹‹የዜጎችን መብት ለማስከበር ወቅቱ የሚፈልጋቸው ጉዳዮችን በመገንዘብ የሚናበብና የሚሠራ ተቋም መፍጠር፣ አሰራሮቹንም መፈተሽ ያስፈልጋል›› ብለዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም በመሆኑ ኅብረተሰቡ ጥቆማዎችን በመስጠትና ማስረጃ ሆኖ በመቅረብ የቅርብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አመልክተዋል። ከኅብረተሰቡ ጋር የምክክር መድረኮችን መክፈትና ዐቃቢ ሕግ ላይ የነበረዉን ፖለቲካዊ ተጽእኖ እንዳይቀጥል መከላከል አስፈለጊ በመሆኑ ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠይቅም አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ