የውጭ ሀገራት ዜጎች ከኢትዮጵያውያን ጎን በመሆን በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ጫና እያወገዙ ነው።

201
ሕዳር 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አፍሪካዊያን እና የሌሎች አህጉራት ዜጎች በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ እውነታ በመረዳት ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጠ ሲሆን የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ጫና እና ጣልቃ ገብነት በተለያዩ አጋጣሚዎች እያወገዙት መሆኑን ገልጿል።
መግለጫውን የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ “ባለፉት ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ሰልፍ ከመንግሥት ጎን መሆናቸውን አሳይተዋል” ብለዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩት ኢትዮጵያውን ከ27 ሀገራት በላይ ውስጥ ባደረጉት ሰልፍ የውጭ ጣልቃ ገብነት፤ ተገቢ ያልሆነ ጫና እና ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ የሚዲያ ተቋማትን አውግዘዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያከብሩም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ከድጋፍ ሰልፉ በተጨማሪ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በወረራቸው የአማራ እና ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ አሰባስበዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር በመላክ ለሀገራቸው ያላቸውን አለኝታነት ማሳየታቸውንም ጠቅሰዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው የአሜሪካ መንግሥት ኤምባሲ የጸጥታ ስጋት አለ በሚል ዜጎቹ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በተደጋጋሚ የሚያሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ብሏል።
አዲስ አበባ ከተማ እንደወትሮው የጸጥታ ችግር የሌለባት፣ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሁኔታ ላይ የምትገኝ መሆኗን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኤምባሲው ከአሳሳች ድርጊቱ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
“ኤምባሲው በከተማ የጸጥታ ችግር እንዳለ በማስመሰል የሚነዛው መረጃ ዜጎችን ለማሸበር የሚደረግ ጥረት ነው” ብለዋል።
“የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረጉ ጫናዎች አሁንም አሉ” ያሉት አቶ ከበደ፤ ኢትዮጵያውያን በሁሉም አቅጣጫ ለሀገር ሰላም የሚያደርጉትን ሥራ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የአሸባሪውን ኃይል ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ጨምሮ ሌሎች አካላት መኖራቸውም በመግለጫው እንደተገለጸ ኢዜአ ዘግቧል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተገቢ ባልሆነ ሀገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ለስንዴ ወይም ለተያያዥ ድጋፎች ተብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት እና ሉዓላዊነት እንደማይደፈርም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ዜጎች የጠላትን እኩይ ተልዕኮ ለማክሸፍ የሚያደርጉት ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መግለጫውን የሰጡት የሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ጥሪ አስተላልፈዋል።
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየጥር ወር ሙሽራው ሰርጋቸውን በመሰረዝ ወደ ግንባር ሊያቀኑ ነው።
Next articleለወንጀል ድርጊቶች ማስፈፀሚያ ሊውሉ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡