
ሕዳር 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ በርካታ የወገን ኀይሎች የሞራል ስንቅ ማግኘታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። በኹሉም ደረጃ የሚገኙ የወገን ኀይሎችና ሕዝቡ ከጎናቸው በመሰለፍ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይልን ለማጥፋት እየተፋለሙ ነው፡፡
የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ያነጋገራቸው የአማራ ልዩ ኀይል እና የሚሊሻ አባላት የጀግናው መሪ መዝመት ጠላትን በመደምሰስ ዓላማቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል።
ምክትል ኮማንደር በቀለ ጎረምስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀገሪቱ የሕልውና አደጋ ውስጥ በመኾኗ አስፈላጊውን ኹሉ ለማድረግ እስከ ግንባር ድረስ መውረዳቸው የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል። በክፍለ ጦራቸው ውስጥ ከፍተኛ ወኔንና መነቃቃትን መፍጠሩንም ምክትል ኮማንደሩ ጠቁመዋል። “ለሀገር ሉዓላዊነት እና ክብር ምን ያኽል ዋጋ እንደሚሰጠው ከዘማቹ መሪ መማር ይቻላል። ክፍለ ጦራችንም ልክ እንደ ተለመደው ጠላትን እየገረፈው ነው” ብለዋል።

ምክትል ኮማንደሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት የአባቶቻችን የጀግንነት ታሪክ በድጋሜ የታየበት ነውም ብለዋል። ለዘመቻ ብቁ የኾነ ዜጋ ኹሉ በመዝመት ሀገሩን ከተጋረጠባት አደጋ እንዲታደግ ምክትል ኮማንደር በቀለ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምክትል ሳጅን ይንገስ ገበየሁ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት ጠላትን የሚያስደነግጥ ነው ብለዋል። “ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መዝመታቸው ለትግሉ ፍጥነት ወሳኝ ነው፣ ታላቅ አንድምታም ይኖረዋል” ያለው ኮንስታብል ይንገስ፣ ኹነቱ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደኾነላቸውም ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለመላው አፍሪካውያን ተምሳሌት ነው ያሉት ደግሞ ኮንስታብል በላይነህ ዋለ ናቸው። ኹሉም ሕዝብ የሞራል ግዴታ ተሰምቶት እንዲዘምት በር ከፋች መኾኑን ነው የተናገሩት። ኮንስታብል በላይነህ እንዳሉት ኹነቱ የወገን ኀይል በሞራልና በአንድነት ሆኖ ጠላት እንዲደመሰስ እያደረገ ይገኛል።

ኮንስታብል ልዑል ጋሻዬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመታቸው ኹሉም የመንግሥት ባለሥልጣናት ትኩረታቸውን ወደ ግንባር አድርገው ለመደገፍም ኾነ ለመዝመት ፈር ቀዳጅ ኾኖላቸዋል ብለዋል። በተለይ በግንባር የሚገኙ የጦር መኮንኖች ግዴታቸውን በብቃት እንዲወጡ ያስችላቸዋልም ነው ያሉት።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመታቸውን ስሰማ ግርምትን ጭሮብኛል፣ ጠላትን በጋለ ስሜት እንድቀጠቅጠውም ሞራላዊ ግዴታ በውስጤ አድሯል” ብለዋል።
ከደባርቅ ወረዳ ወደ ግንባር ከዘመቱ የሚሊሻ አባላት ውስጥ አቶ ቢያይልኝ ዓለም የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት ሁሉንም የሚያጀግን ነው ብለዋል። ኹነቱ ጠላት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠፋ ያስችላልም ነው ያሉት።
“የሀገሪቱ ቁንጮ መሪ መዝመታቸው ኹሉም ዜጋ ሰበብ ሳይፈጥር እንዲዘምት ሞራላዊ ጫናን ይፈጥራል” ያሉት አቶ ቢያይልኝ በጋለ ስሜት ኾነው ጠላትን እያስወገዱ እንደኾነ አስረድተዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ-ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ