
አዲስ አበባ፡ ሕዳር 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በመግለጫቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የክተት ጥሪዉ ላይ መሳተፍ ይገባዋልም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በግንባር አመራር እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲ አባላት አርቲስቶች እና አትሌቶችም ወደ ግንባር መዝመታቸዉን በመግለጫቸዉ አንስተዋል። ጊዜዉ ሀገራዊ ግዴታ የምንወጣበት በመሆኑ ወደ ግንባር ያልዘመተ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሻሻል በአግባቡ ሥራውን በማከናወን የበኩሉን መወጣት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
እየተካሄደ ያለው ትግል የመላው ጥቁር ሕዝቦች ነው ያሉት ዶክተር ለገሰ ሁሉም አፍሪካውያን ትግሉን እንዲቀላሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች በነጻነት እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ 11ኛ ክልል መሆኑን ተናግረዋል።
ዶክተር ለገሰ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ በተሠሩ ተግባራት ላይ በሰጡት መግለጫም በአዲስ አበባ እና በዙሪያዉ የሽብር እንቅስቃሴ ሊያካሄዱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዉለዋል ብለዋል። በፍተሻም ተቀጣጣይ ቦንብ የሬዲዮ መገናኛ፣ የጸጥታ አካላት ዪኒፎርም እና በከተማዋ ሊካሄድ የታሰበ የሽብር ድርጊት ዝርዝር መረጃ በቁጥጥር ስር ዉሏል ነው ያሉት።
“ዣን አፍሪካ” የተባለ መጽሔት ከፕሬዚደንት ሳህለ ወርቅ ዘዉዴ ጋር አያይዞ ያቀረበዉ መረጃ ኃላፊነት የጎደለዉና በአመራሩ መካከል ክፍፍል አለ የሚለዉ ሐሰተኛ መረጃ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉዑሽ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ