
ሕዳር 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር በተለያዩ ጊዜያት አደጋ ላይ በገባች ጊዜ መሪዎች ጦራቸውን ግንባር ኾነው በመምራት ወርቃማ ድል አስመዝግበዋል። በአድዋ ጦርነት የአጼ ሚኒሊክን እና የእቴጌ ጣይቱን በጦር ግንባር የፈጸሙትን የአመራር ጥበብ ማንሳት ይቻላል። በአድዋ የነገስታቱን ግንባር መዝመት አነሳን እንጂ በየጊዜው የነገሱ ነገስታቶች እና የሀገር መሪዎች ጦራቸውን ግንባር ድረስ በመምራት ተዋግተዋል፤ አዋግተዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶክተር) ሀገሪቱ በውስጥ እና በውጭ ኀይሎች የተሰነዘረባትን የተቀናጀ ጥቃት በመቀልበስ ደማቅ ገድል እንድትጽፍ ግንባር ዘምተዋል።
ኮንስታብል ፋሲል አለልኝ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር መቀላቀል ከነበራቸው ወታደራዊ ወኔ በላይ እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል። የአሸናፊነት ስሜት ፈጥሯልም ነው ያሉት። እንኳን ግንባር ለዘመተው ሠራዊት ለመዝመት ለተዘጋጁ ወጣቶችም ሞራል እና ወኔ እንደሚፈጥር ነው የገለጹት። የደጀኑ ሕዝብም በግንባር ለሚዋደቀው ሠራዊት የሚያደርገውን እገዛ የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል።
ኮንስታብል ታደሰ በዜ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር መዝመት የሠራዊቱን ወኔ የበለጠ እንዲነሳሳና በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል የሚኖረውን መስተጋብር የበለጠ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
ሠራዊቱ ሀገርን ለማገልገል ከገባው ግዳጅ በላይ ወኔ ተላብሶ ለመፋለም ትልቅ ስሜት መፍጠሩንም ገልጸዋል። አንድ የሀገር መሪ ግንባር ሲዘምት የደጀኑ ሕዝብም በገንዘቡ እና በስንቅ ዝግጅት ሥራ የበለጠ እገዛ እንዲያደርግ ያግዛል ነው ያሉት።
ኮንስታብል ሰላም ዘመነ የጠቅላይ ሚንስትሩ ግንባር መቀላቀል ሠራዊቱ ግዳጁን የበለጠ እንዲወጣ ወኔ ፈጥሯል። አሸባሪውን ቡድን ከገባበት ገብቶ ለመደምሰስ ዝግጁ እንዲኾኑ እንዳደረጋቸውም ለአሚኮ ተናግረዋል።
ምክትል ሳጅን ኪሮስ ሞላ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር መሰለፍ የፈጠረው ወኔ በአጭር ጊዜ የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ያግዛል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ