
ሕዳር 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በከተሞች በኅብረተሰቡ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች በመመሳሰል እንዲገቡ በማድረግ አዲስ አበባ እና በዙሪያው ተልእኮ ሰጥቶ በማስገባት ለሽብር ተግባር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን እንደተደረሰበት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ገልጸዋል።
የሽብር ኃይሉ አባላቱን በንግድ ተቋማት፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና በሌሎችም የሙያ ሥራዎች ኅብረተሰቡ ውስጥ ተሰግስገው እንዲገቡ በማድረግ አዲስ አበባን እና አካባቢውን ለማተራመስ ማቀዳቸው ተደርሶበት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ወራሪው ኃይል ለሽብር ተልእኮ ያሰማራቸው በርካታ ግለሰቦች በርካታ ተተኳሽ ጥይቶች ከነፍስ ወከፍ እና የቡድን የጦር መሳሪያ ማለትም ቦንቦች ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ገንዘቦችን ይዘው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አብራርተዋል።
የተለያዩ የክልል እና የፌዴራል የፀጥታ መዋቅር አልባሳትን ከነዓርማው በማልበስና የተለያዩ የጦር ሜዳ መነፅር እና ሌሎችንም ቁሳቁሶችን በመጠቀም አሳሳስቶ ለመልበስ መሞከሩን ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ ማገኘቱን ገልጸዋል።
ሐሰተኛ መታወቂያ ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ማህተሞችንና ቁሳቁሶችም ተይዘዋል ተብሏል።
ይሄንን ኃይል መንጥሮ ማውጣቱ የፀጥታ ግብረ ኃይሉ ዋነኛ ተግባር ቢሆንም የኅብረተሰቡ ድጋፍ አሁንም ከተጀመረው በላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ኅብረተሰቡ ፀጉረ ልውጦችን ሲያይ በመጠቆም የያዘውን መታወቂያ ትክክለኛነት ማጣራትም እንዳለበት ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ አሳስበዋል።
አካባቢህን ጠብቅ!
መሪህን ተከተል!!
ሀገርህን አድን!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ