
ሕዳር 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሠንደቁ ውስጥ ቃል ኪዳን አለበት ፈጣሪና ኢትዮጵያውያን የተሣሠሩበት ፣ በሠንደቁ ውስጥ ምስጢር አለበት ተመርምሮ ያልተደረሰበት፣ በሠንደቁ ውስጥ ተስፋ አለበት ጭቁኖች ሁሉ የሚጠብቁት፣ በሠንደቁ ውስጥ ድል አለበት ጠላት የሚገረሰስበት፣ በሠንደቁ ውስጥ ኃይል አለበት ሁሉም የሚገዛለት፣ በሠንደቁ ውስጥ እውነት አለበት እውነተኛው የተቀመጠበት፣ እውነተኛውን ያስቀመጠበት፣ በሠንደቁ ውስጥ ቅዱስ መንፈስ አለበት እርኩስ መንፈስ የሚርቅበት፣ መለያየት የሚሞትበት፣ ጥል የሚቀበርበት ፣ አንድነት የሚነሳበት፣ ኃያልነት የሚገንበት። በሰማይ የተቀለመ፣ በልብ ውስጥ የታተመ፣ ከሁሉም በፊት የቀደመ፣ የተስፋውን መንገድ የተለመ።
በሰማይ የሚውለበለብን፣ በሰማይ የከበረን፣ ከዘመናት በፊት የነበረን፣ ያለን፣ የሚኖርን ተስፋ የሆነን፣ የሚሆንን ሠንደቅ ማን ችሎ ያጠፋል? ማንስ ችሎ ከወሰኑ ያልፋል? በሰማይ የከበረውን በምድር የሚያዋርደው የለም። ይልቅስ ላዋርድ ካለ በሰማይ ያለው የምድሩን ያዋርደዋል እንጂ።
በሠንደቁ ውስጥ ጠላቶች የማያውቁት፣ ባለቤቶቹ የሚመኩበት ኃይል አለ። በአንድነት የሚያሰበሳብ፣ ለአንዲት፣ ለፀናች ሀገር የሚያስብ። በሠንደቁ ውስጥ ጥበብ አለ ችግር የሚፈታ፣ በሠንደቁ ውስጥ ጀግንነት አለ ጠላትን የሚረታ፣ በሠንደቁ ውስጥ ኃያልነት አለ በክፋት የተነሱትን ሁሉ በቁጣ የሚመታ።
ሠንደቁ ተነክቶባቸው በቁጣ የተነሱት ሁሉ በድል ተመልሰዋል። ጠላቶቻቸውን አጥፍተው በድል አድራጊነት ፎክረዋል፣ በጀብደኝነት ተንጎማለዋል። ሠንደቃቸውን ከፍ አድርገው አውለብልበዋል። ከሠንደቁ ግርጌ በሠንደቁ ፍቅር አልቅሰዋል። ሠንደቁን የነካውን ሁሉ ሊቀጡት ቃል ኪዳን አሥረዋል። ሠንደቁ የማሸነፊያ ምስጢራቸው፣ የሚመኩበት ምልክታቸው፣ ከጠላት ጦር የሚድኑበት ጋሻቸው፣ ጠላትን የሚወጉበት ጦራቸው፣ የሚቆርጡበት ሰይፋቸው፣ የሚተሳሰሩበት ገመዳቸው፣ የሚጠለሉበት ጥላቸው፣ ብርሃን የሚያዩበት ብርሃናቸው፣ የሚደምቁበት ጌጣቸው፣ የሚግባቡበት ቋንቋቸው፣ የሚዘምሩት ዜማቸው ነው። ለሠንደቁ መሞት፣ ለሠንደቁ መሰጠት ያውቁበታል።

ቀደም ባለው ጊዜ ጀምሮ ቀደምቲቷን ሀገር ኢትዮጵያ ጠላቶቿ እጃቸውን አንስተውባታል። ሊወጓት ጦር አዝምተዋል፣ ሊያጠፏት ዶልተዋል፣ ሊያፈርሷት ተማክረዋል፣ ግንባር ፈጥረዋል። ዳሩ ጦር ያዘመቱት፣ የዶለቱት፣ ግንባር የፈጠሩት፣ በድብቅ ሐሳብ የመከሩትም ጠፍተዋል። ለአሸናፊነት ብቻ የተፈጠረች ናትና እያሸነፈች እየጣለቻቸው ቀጠለች። በጦር የመጣውን ሁሉ በጦር እየቀጣች የማትደፈር መሆኗን አሳየች።
ነጭ ከፈጣሪ ቀጥሎ አምላክ በሚመስለበት ዘመን ጥቁሮች እየታደኑ ይታሰሩ፣ ይገረፉ፣ እንደ እቃም ይሸጡ ነበር። ነጮች ከወሰናቸው እየተነሱ፣ የጥቁሮችን ቀዬ እያሰሱ ባለሀገሮችን ሀገር አልባ ያደርጉ ነበር። በየብስና በባሕር አቆራርጠው የሚመጡት ነጮች የጥቁሮችን ምድር የመከራ፣ የስቃይ፣ የፍዳ ምድር አደረጓት። ያለ ከልካይ ተቀራመጧት። ታዲያ በዚያ ዘመንም ሆነ በቀደመው ዘመን በታላቅነት የቀጠለች አንዲት ድንቅ ሀገር ብቻ ዳሯን እሳት አድርጋ ተቀመጠች። የጥቁርን ብርሃን እያጠፉ የመጡት ነጮች በአፍሪካ ምድር በምሥራቅ ንፍቅ ከምትገኝ ቀደምት ሀገር ውጭ አፍሪካን የጨላማ ዓለም አደረጓት። በምሥራቅ ንፍቅ እያበራች ለምዕራቡ፣ ለሰሜኑና ለደቡቡ የአፍሪካ ሀገር ምልክት የምትሰጠዋን ሀገርም ጨርሰው ሊያጠፏት መጡ። እርሷ ብቻ በጨለማ ውስጥ የምትታይ ብርሃን ነበረችና። ጨለማ ውስጥ የምታበረዋን ብርሃን ሊያጠፏት ጦር ሰብቀው ከተፍ አሉ። በአሻገር የምትታየው ብርሃን ግን በቀላሉ የምትጠፋ አልነበረችም። መጥተው ሞከሯት። ክንዷን አሳየቻቸው፣ እንኳንስ ልትጠፋላቸው፣ መላውን አፍሪካ አብርታ በጨለማ ውስጥ የደበቁትን ገመናቸውን ገለጠችባቸው። አጥፊዎቿን አጥፋታ የበለጠ ብርሃኗን ጨመረች። በመድፈኛው ንጉሥ የተላኩትን ወራሪዎች በፈረሰኛው ንጉሥ ምኒልክ የተመሩት ጀግኖች አሸንፈው ጨለማ ያጠላበትን ምድር ነብስ ዘሩበት፣ ብርሃን አሳዩበት፣ በምሥራቅ ብቻ ሲበራ የነበረው ብርሃን በየአቅጣጫው ተንቦገቦገ። በምሥራቅ ፀሐይ ወጣ እንዳለ መፅሐፍ በምሥራቅ ፀሐይ ወጣ፣ በምሥራቅ ነፃነት መጣ። ዓድዋም ከተራራ በላይ ገዘፈ። ስሙ በታሪክ ድርሳን ከፍ ብሎ ተፃፈ።
ከሌሎች ተራራዎች ተለይቶ በደም ማህተም የተቀረፀበት ድል ያለበት፣ የነፃነት መዝሙር የተዘመረበት፣ ከዳር እስከ ዳር ብርሃን የታየበት ኃያል ሆነ። በተቀደሰችው ምድር በኢትዮጵያ እንዳይውለበለብ የተፈለገው ሠንደቅ የበለጠ ከፍ አለ። የኢትዮጵያ ጠላቶች ቀደም ሲል በዓድዋ ዘመን በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚወለበለበውን ሠንደቅ ነካክተው፣ በመላ አፍሪካ እንዲውለበለብ አደረጉት፣ እነርሱን ጠርጎ ብርሃን ተካባት፣ የጥቁርን ዘር ሁሉ ነፃ አወጣበት። ሠንደቁን ነኩት፣ አስቆጡት። ሁሉም የጥቁር ዘር ይሄስ ነፃነት ነው እያለ ወራሪን እየፈነገለ በየሀገሩ ያውለበልበው ጀመር። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ የአፍሪካውያን መለያ፣ ምልክት ሆነ። በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እንከልክልህ ሲሉት ይባስ ብሎ በአፍሪካ ሀገራት ተውለበለበና አስገረማቸው፣ አስደነገጣቸው፣ ነቃቅሎ ጣላቸው፣ ጠራርጎ አጠፋቸው፣ ማዕበል ሆኖ ወሰዳቸው።

ዓመታት አልፈው ዓመታት ተተኩ። ያደፈጡት የኢትዮጵያ ጠላቶችም ጊዜ ጠብቀው ተነሱ። እንደ ቀደመው ሁሉ በአራት አውታር ወጥረው ወደ ፊት ስትል ደረቷን፣ ወደኋላ ስትል ጀርበዋን፣ ወደ ላይ ስትል ራሷን፣ ወደታች ስትል እግሯን ሊወጓት ተጠራሩ። ያን የነፃነት ምልክት፣ ነፃ የሆኑ ሕዝቦች የሚመኩበትን ሠንደቅ በምድሯ ላይ እንዳይውለበለብ መከሩ። ታምረኛው ሠንዳድ ግን የበለጠ ሰፋባቸው። ሠንደቁን ለማጥፋት የከጀላቸው እልፍ ሆኖ ደረሰ ከደጃቸው። ዛሬ ላይ ድጋሜ ቢነኩት ከአፍሪካ ተሻግሮ በመላው ዓለም እንዲውለበለብ አደረጉት። የዓለም ሕዝቦች በጎዳናዎች ሲወጡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ታያቸው፣ ዓይናቸውን ያዛቸው፣ ልባቸውን ሰቀዛቸው፣ ዘወር ብለው አውታራቸውን ሲከፍቱ ሠንደቁ ተጥለቅልቋል፣ ቀና ቢሉም በሰማዩ ላይ ያለው ቀለም ያው ብቻ ሆኗል። አስጨነቃቸው፣ ሰንጎ ያዛቸው። ከኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ፣ ከአፍሪካ ወደ ዓለም ሰፋባቸውና ተገረሙ።
ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “በሰማዩ ላይ ቢታይ ቀለም፣ የእርሷ ነው እንጂ ሌላ አይደለም” ብሎ የተቀኘላት ድንቅ ጥበብ ያረፈበት ማሸነፊያ ነው። እነርሱ ደምና አጥንት ተከፍሎበት በተውለበለበት ቅድስት ምድር ሊያጠፉት ቢመኙም በእነርሱው ሰማይ ሥር ሲውብለበለብ ዋለ። የራቀው ቀረባቸው፣ የደበዘዘ የመሰላቸው ጎላባቸው፣ የጠፋ የመሰላቸው ደመቀባቸው፣ ያጠፉት የመሰላቸው ሊያጠፋቸው ገሰገሰባቸው፣ ኃይሉ ረቂቅ ነውና የሚችለው የለም። የምስጢሩን ምልክት፣ የሚችሉት ምስጢራዊያን ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያን ለማፍረስ፣ ኢትዮጵያውያንንም ለማሳነስ የተነሱት ሀገራት በየከተሞቻቸው ጎዳናዎች አትንኩኝ የሚለው ሠንደቅ አጥለቀለቃቸው። ከደጃቸው ድረስ ሄደ። ከታሪክ ድርሳናት ላይ ቢያጠፏት የሚወዷት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየተጠራች፣ አትንኳት፣ አትንኩን እየተባለች ረፍት ነሳቻቸው። የጀግና ልጆቿ ድምፅ አስደነገጣቸው። የማትነካውን ነክተዋል፣ የማትቻለዋን ገፍተዋልና እረፉ አሏቸው። የዓለም ከተሞች አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም የተቀቡ እስኪመስል ድረስ አሸበረቁ። ጎዳናዎች ተጨነቁ።
ሠንደቁን አትንኩት፣ ከነካችሁት ይሰፋል እንጂ አይጠብም፣ ይጠነክራል እንጂ አይደክምም፣ ይደምቃል እንጂ አይጠወልግም፣ ይፋጃል እንጂ አይቀዘቅዝም፣ ማዕበል ሆኖ ይወስዳል እንጆ ምንጩ አይደክምም። ሲነኩት የሚሰፋ ምስጢሩም የማይረዱት ረቂቅ ነውና አትንኩት። የነኩት ከኢትዮጵያ ሰማይ ባሻገር በመላው ዓለም እንዲውለበለብ አደረጉት። ይህ ሠንደቅ እንደነርሱ አሁን የተፈጠረ አይደለም። አስቀድሞ የነበረ፣ ከምንም እና ከማንም የጠነከረ፣ በሰማይም በምድርም የተከበረ ነውና ሲነኩት አይወድም። ምንም ቢሆን ከከፍታው አይወርድም።

አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን የአሸናፊዎችና የጀብደኞች ሠንደቅ ይዞ የተነሳ ሁሉ ያሸንፋል፤ ወጀቡን ያልፋል። ታሪኩን ከፍ አድርጎ ይፅፋል። አንድ ነገር አስታውስ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ስለ እውነት ተነስተው ተሸንፈው እንደማያውቁ፣ አንድ ነገር አምነህ ተነስ፣ ወደፊትም ገስግሰው የኢትዮጵያን ስም ጠርተህ፣ ሠንደቁን አሸንፈህ እንደምትመለስ። የሀገራትን ጎዳናዎች ያስጨነቀው ሠንደው በመንፈሳቸውም ገብቶ ያስጨንቃቸዋልና አንድ ሆነህ ታገል፣ ድል ከአንተ ጋር ነው። ከምንም የጠነከረ አንድነት ፈጥረህ እስከታገልክ ድረስ አሸናፊው አንተ ብቻ ነህ። ሠንደቁን አስቀድመህ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የበቀለውን ጠላት ለማጥፋት ገስግስ።
በታርቆ ክንዴ
ያለ መስዋእትነት ድል አይገኝም!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ