“ሕዝብ እና መንግሥት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከውጭ ጠላቶች እና የውስጥ የሽብር ቡድኖች ጋር ግልፅ ትንቅንቅ ውስጥ ገብተዋል” ዶክተር አብርሀም በላይ

221
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አብርሀም በላይ (ዶ.ር) ሕዝብ እና መንግሥት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከውጭ ጠላቶች እና የውስጥ የሽብር ቡድኖች ጋር ግልፅ ትንቅንቅ ውስጥ መግባታቸውን ገልፀዋል።
ዶክተር አብርሀም በላይ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
መልእክቱም እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ሕዝባችን እና መንግሥታችን ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተከፈቱትን ዘርፈ ብዙ የውጊያ አውዶች በሚገባ አጥርተው ለይተው ራስን የመከላከልና የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ለማስጠበቅና ለማስከበር ከውጭ ጠላቶች እና የውስጥ የሽብር ቡድኖችና ባንዳዎች ጋር ግልፅ ትንቅንቅ ውስጥ ገብተዋል።
ይህንን የተናበበና የመጨረሻ ግቡ የተዳከመችና ጥቅሞችዋን ለማስጠበቅ የማትችል ደካማ ሀገር የማረጋገጥ ፍላጎት፣ የተበተነና በግዛትም ጭምር የተከፋፈለ ሕዝብና ሀገር የማስፈን ቅዠት፣ የቀጣናውን ያለመረጋጋትና አለመተማመን በመጠቀም ለዓመታት የሚዘልቅ ኢ ፍትሐዊ የብሔራዊ ጥቅሞችን የማቋቋምና የማደላደል ሴራ ስሪት ግልፅ እሽቅድምድም፣ በታላቅ ሕዝባዊ ይሁንታ ከመጣው የኢፌዴሪ መንግሥትና በታሪኩ፣ በማንነቱ፣ በጀግንነትና በፅኑ ተምሳሌታዊ ገድሎቹ ደምቆ በነቂስ በከተተውና በደጀንነት በተሰለፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ፀሐይ የሞቀው ገሐድ ጉዳይ ነው።
መከላከያ ሠራዊታችን፣ የሚሊሻ፣ ልዩ ኃይልና አጋዥ ሕዝባዊ የፀጥታ አደረጃጀቶቻችን በሀገር ውስጥና በውጪ ካለው ደጀን ሕዝባችን ጋር በመቀናጀት ለክተቱ እየሰጡ ያለው ፈጣን ምላሽ አኩሪ ነው።
ይህንን በውጊያ፣ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲሁም በሚዲያና የሥነ-ልቦና ጫና ጭምር የሚገለፅ ጦርነትና በሁሉም አቅጣጫ የሚዘንበውን ጥቃት መንግሥትና ሕዝባችን በተገቢው በመመከት የአባቶቹን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ለመድገም በአንድ ተሰልፏል።
ባንዳው የሽብር ቡድኑ ሕወሓት የጥፋት ጀሌዎቹና ሸኔ ከውስጥ፣ በታሪካዊ ጠላትነታቸው የፀኑና ጥቅም መር ፍላጎታቸውን በጉልበት ለመጫን የሚታትሩ ግልፅ የውጭ ጣልቃ ገብ ኃይሎች መንግሥትና ሕዝባችን አምርረው የሚታገሏቸው ጠላቶቻችን ናቸው!!
ድል ለፍትሐዊ እና ተምሳሌታዊ ተጋድሎአችን!
Previous article❝ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ደኅንነት የምንሰስተው ሕይወት የለምና እኛም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዘምታለን❞አቶ ክርስቲያን ታደለ
Next article“የዳግማዊ ዓድዋን ታሪክ የምንፅፍበት ወሳኙ ምእራፍ ላይ ነን፤ያለጥርጥር ደማቅ ታሪክም እንፅፋለን” የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ