አቅሙ የደረሰ አማራ ሁሉ ለህልውናው፣ ለነጻነቱ እና ለክብሩ መዝመት አለበት።

253
ሕዳር 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የክተት ጥሪውን የተቀበሉ የመቄት ወረዳና የፍላቂት ገረገራ ከተማ ወጣቶች እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ዘመቻውን መቀላቀል የሚያስችል ወታደራዊ ዝግጅት አድርገዋል። ዝግጅቱን ያደረጉት በግንባሩ በተሰለፈው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ነው። ግንባሩን ለመቀላቀል በራሳቸው ተነሳሽነት የተዘጋጁት ወጣቶችና የመንግሥት ሠራተኞች በአጭር ጊዜ ማንኛውንም ወታደራዊ ግዳጅ መፈጸም የሚያስችል ስልጠና መውሰዳቸውን ኮሎኔል ደሳለኝ ተሰማ ተናግረዋል።
ጠላት በሕዝባዊ ማዕበል እየፈጸመ ያለውን ወረራ ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ አቅሙ የፈቀደ ሁሉ በግንባር ሊታገል እንደሚገባም አንስተዋል። ዘማቾች መሠረታዊ ወታደር ማግኘት ያለበትን ዕውቀት እንዲያገኙ መደረጉ የአባቶቻችንን ታሪክ በጠንካራ ክንዳችን በማስቀጠሉ ሂደት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፤ የተሻለ ተነሳሽነትም ይፈጥራል ብለዋል። የሚሰጣቸውን ስምሪት በታላቅ ሀገራዊ ፍቅር እና በላቀ የጀግንነት ስሜት እንደሚፈጽሙም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተስፋሁን ባታብል (ዳቆን) ጠላት በአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው በደል የከፋ መኾኑን ጠቅሰዋል። ሀገር ለማፍረስና የአማራን አንገት ለማስደፋት ከሕጻናት እስከ አዛውንት፣ ከመነኩሴ እስከ መሻሂ፣ ከእረኛ እስከ ምሑር እያሰለፈ ነው። “እኛም እንደ ሕዝብ ፊት ለፊት ታግለን ለትውልድ ነጻነትን እናጎናጽፋለን” ብለዋል።
ጠላት ከገባበት እንዳይወጣ መሪዎች ከፊት ተሰልፈው ሚናቸውን እየተወጡ እንደኾነም ተናግረዋል። አስተዳዳሪው እንዳሉት ጠላትን በፍጥነት ለማጥፋት አቅሙ የደረሰ አማራ ሁሉ ለህልውናው፣ ለነጻነቱ እና ለክብሩ መዝመት ይኖርበታል። ሰልጣኞችም ግንባር ላይ ያለውን ኀይል ይቀላቀላሉ፤ ጠላት ሙሉ በሙሉ እስከሚጠፋ ይህ ተግባርም ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ለዘመቻው ከተዘጋጁት መካከል መምሕር አሥራት ኀይለማርያም ያስተምርበት የነበረው ትምህርት ቤት በአሸባሪዎቹ ወድሟል። የአካባቢውን ሕዝብ ሁለንተናዊ ስብዕና ለማበላሸት በማሰብም በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ በደል ተፈጽሟል። የትምህርት ቤቱ ቁሳቁስ ተሟልቶ ሥራ እስከሚጀመር እና ሰው በሰብዓዊነቱ ተከብሮ በነጻነት መኖር የሚችልበት ሁኔታ እስኪፈጠር የትግሉ አካል ለመሆን መወሰኑን ገልጿል።
ጠላት በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ሁለንተናዊ ጫና ለመቀልበስ እስከመጨረሻው የድርሻውን እንደሚወጣም መምህሩ ተናግሯል።
ከውትድርና ሕይወቱ በግፍ የተባረረው ወታደር ደሳለኝ አባይነውም ለስቃይ የዳረገውን አሸባሪ ኀይል ለማጥፋት ዳግም ተዘጋጅቷል።
ሌሎች አስተያየታቸውን የሰጡን ወጣቶችም ጠላት እስኪጠፋ ለመታገል ቆራጥ አቋም መያዛቸውን ተናግረዋል።
በመጀመሪያው ዙር ሰልጥነው ግንባር ከተሰለፉ ወጣቶች መካከልም ምሽግ የሰበሩና ከጠላት ትጥቅ በመቀማት ጀብድ የፈጸሙ ይገኙበታል። እነዚህ ወጣቶች አካባቢው የጀግኖች መፍለቂያ መሆኑን በተግባር ያስመሰከሩ ናቸው።
የወረዳው ማኅበረሰብ ለሠራዊቱ የማያቋርጥ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም በመርሃ ግብሩ ተጠቅሷል። ይህም ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና በተባበረ ክንድ ተቀልብሶ ወደነበረችበት ሰላም የምትመለስበትን ጊዜ ቅርብ እንደሚያደርገው ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ-ከመቄት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ጽናት ካለ ድንጋይና መጥረቢያም ቦምብ ነው”
Next articleአሜሪካዊቷ ሴናተር ሼላ ጃክሰን ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጎን እንደሚቆሙ አስታወቁ።