“ጽናት ካለ ድንጋይና መጥረቢያም ቦምብ ነው”

226
ሕዳር 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዋግሹሞችን አንግሳለች፣ የወራሪውን ጣሊያን ጦር እንደ እግር እሳት የለበለቡትን ሌተናል ጀነራል ኀይሉ ከበደን አፍርታለች፤ የጀግና ልጅ ጀግና ነውና ዛሬም ጀግኖችን ተክታለች፤ ዋግ ኽምራ።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በዞኑ ባደረሰው የንብረት ውድመት እና የንጹሃን ግድያ የዋግ አናብስቶች ቁጭት ውስጥ ገብተዋል። በዚህም ግርማ ሞገስ ተላብሰው የተሰደሩ ሰንሰለታማ ተራሮችን እና እነዚህን ሰንሰለቶች ተከትለው የተዘረጉ ሸለቆዎችን እንደ ደጀን በመጠቀም ጠላትን በመለብለብ ጀግንነታቸውን አሳይተዋል፤ እያሳዩም ይገኛሉ።
ከእነዚህ ጀግኖች ውስጥ ደግሞ አርሶ አደር ወንድሙ ዘሪኹን አንዱ ናቸው። አርሶ አደር ወንድሙ በሽብር ቡድኑ ድርጊት ተቆጭተዋል። በዚህ ስሜት ውስጥ እንዳሉም ሃምሳ የሚኾኑ የወራሪው አባላት ወደ አሉበት በመሄድ የወገን ጦር ያለበትን ቦታ እንዲያሳያቸው ጠየቋቸው። አቶ ወንድሙ ግን የወገን ጦር ያለበን ቦታ ለመናገር ፈቃደኛ አልኾኑም። በዚህ የተበሳጩት የሽብር ቡድኑ አባላት አቶ ወንድሙን ለመግደል ሲነጋገሩ ሰሙ። ወዲያውኑም ከሽብር ቡድኑ በጥበብ አመለጡ።
አርሶ አደሩ ከተደገሰላቸው ግድያ አምልጠው ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ የሽብር ቡድኑ አንድ አባል ከአካባቢው ማሕበረሰብ ለአባሉ ምግብ እያስገደደ ሲያሰባስብ ቆይቶ በአንድ አርሶ አደር የሰብል ስብሰባ ድግስ ላይ አገኙት። አቶ ወንድሙ ከየት እንደመጣ በሁለተኛ ቋንቋነት በሚጠቀሙበት በትግረኛ ጠየቁት። የሽብር ቡድኑ አባል መኾኑን እና ምግብ በማሰባሰብ ላይ እንዳለ ከጓደኞቹ መነጠሉን ነገራቸው።
አሸባሪ ቡድኑ በወገኖቻቸው ላይ በፈጸመው ግድያ፣ ዘረፋና ስደት የበገኑት አርሶ አደር ወንድሙ ተበሳጭተው የወገን ጦር ያለበትን ቦታ ማጣራት ጀመሩ። የወገን ጦር ያለበትን ቦታ ካረጋገጡ በኋላ ወደ አሸባሪው አባል ተጠግተው “ና በል እምወድህ፣ ከጓደኞችህ ልደርብህ” ብለው የወገን ጦር ወዳለበት ይዘውት መጓዝ ጀመሩ። የወገን ጦር ካለበት አካባቢ ሲደርሱ ግን ያልታሰበ ነገር ገጠማቸው፤ ብሬን ካጠመደ ቆፍጣና የአማራ ልዩ ኀይል፣ ቁም!! የሚል ድምጽ። አቶ ወንድሙም ፈጠን ብለው “ገበሬ ነኝ፤ እንዳትመታኝ፣ ወገን ነኝ” ሲሉ መለሱለት። ይህንን የሰማው ጠላት በጩኸት “ልታስገድለኝ ከአማራ ወታደር ታመጣኛለህ?” ብሎ ወደ ኋላ ሸሸ። አርሶ አደሩም እንዲቆም ጠየቁት። የሽብር ቡድኑ አባል ለማምለጥ ሲንደፋደፍ ጭንቅላቱን በመጥረቢያ መትተው ጣሉት። ተንከባሎ ለማምለጥ ሞከረ። አቶ ወንድሙም እንደ ተቆጣ ነብር ዘለው ተከመሩበት። ለደቂቃዎች ትንቅንቅ ከተደረገ በኋላም የአሸባሪውን አባል በድንጋይ ጭንቅላቱን መትተው ጣሉት። ከወደቀበት ላይም ጭንቅላቱን በድንጋይ ደጋግመው በመምታት በአካባቢው ነዋሪዎችን እያስገደደ ምግብ ይነጥቅ የነበረውን የወራሪ አባል እስከወዲያኛው ሸኙት።
አርሶ አደሩም በአካባቢው ለሚገኘው የወገን ጦር አሸባሪ መግደላቸውን በመንገር የትጥቅ ባለቤት ኾኑ። በቀጣይም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይልን ከወገን ጦር ጋር በመቀናጀት ለመፋለም መዘጋጀታቸውን ነው አቶ ወንድሙ የነገሩን።
ወኔው ካለ በጎራዴም ጠላትን እንደ እግር እሳት ማቃጠል እንደሚቻልም ገልጸዋል።
የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ነጋ ጉልሽ አቶ መንድሙ ለሰሩት ጀብድ የወረዳው አስተዳደር የትጥቅ ሽልማት ማበርከቱን ገልጸዋል። ሌሎች ሚሊሻዎችም ጠላትን በደፈጣ እያርበደበዱት እንደሚገኙ አቶ ነጋ ነግረውናል።
በተደረገው ተጋድሎም የሽብር ቡድኑ ከአካባቢው ነዋሪዎች የዘረፈውን 145 ሺህ ብር ማስቀረት መቻሉን እና ጠላትን በመደምሰስ በርካታ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መማረክ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
አባቶቻችን የጣሊያንን ጦር ያሸነፉት ከጠላት ጋር የሚመጣጠን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቀው ሳይኾን በጀግንነትና በወኔ በጋሻ እየመከቱ በጦር እና በጎራዴ በመፋለም እንደኾነ ያነሱት አቶ ነጋ ወጣቶች በመደራጀት ጠላትን መቀመጫ ሊነሱት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያሉትን ጫና በመቃወም ሰልፍ እያካሄዱ ነው፡፡
Next articleአቅሙ የደረሰ አማራ ሁሉ ለህልውናው፣ ለነጻነቱ እና ለክብሩ መዝመት አለበት።