
ሕዳር 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ጦርነቱን ፈርታ ሳይሆን ጠልታ የዛሬዎቹን ሽብርተኞች እና የያኔዎቹን እብሪተኞች ደግማ እና ደጋግማ የሚመጣውን በማሰብ ለምና አስለምናቸው ነበር፡፡ እናቶች ስለልጆቻቸው ደኅንነት እና ስለሀገራቸው ሰላም ሲሉ ከፊታቸው ተደፍተው እያለቀሱ ለምነዋቸው እንደነበር አይረሳም፡፡ የሃይማኖት አባቶች አባታዊ ግዴታቸው እና ሃይማኖታዊ ተልዕኳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለሀገር መቀጠል ሲሉ ጠርተው ሳይሆን ሄደው ከመገሰጽ አልፈው ተማጽነዋቸው እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነበር፡፡
ታላላቅ የሀገር ባለውለታዎች “አመጣጣችን ከመለያየት ይልቅ በአብሮነት የተገመደ ነውና ስለሀገር ስትሉ ተው” ሲሏቸው እያፌዙ “ሀገር በሽማግሌም በሽምግልናም አትመራም” ያሉትኮ እነርሱ ነበሩ፡፡ ዳሩ ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ በሽምግልና ዘመናቸው ጦር ሰብቀው ኢትየጵያውያንን ሊወጉ የመጡትም እነርሱ ነበሩ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር መንግሥት ተገዶ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ውስጥ የገባው፡፡ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ምንም እንኳን ሽብርተኛው ትህነግ ለጦርነት ቀድሞ ሲዘጋጅ ቢቆይም የኢትዮጵያውያንን ጠንካራ ክንድ ለመቋቋም የቻለው ከሦስት ሳምንታት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ተጭኖት የነበረውን የጭቆና ቀንበር ምንጩም ሆነ ባለቤቱ ሽብርተኛው ትህነግ እንደሆነ ካለምንም ብዥታ ያውቃል፡፡ ጭቆናን ጠልቶም ባዶ እጁን አደባባይ ወጥቶ ግንባሩን እና ደረቱን ለእብሪተኞቹ ጥይት ሰጥቶ ታግሎ ጥሏቸዋል፡፡ ቀስ በቀስም ቢሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትናንቱን ጭቆና መልሶ ሊጭንበት እየተፍጨረጨረ ያለው ጥንተ ጠላቱ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ብቻ እንደሆነ ያምናል፡፡

መንግሥት ከወራት የሕግ ማስከበር ቆይታ በኋላ ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት የተኩስ አቁም ውሳኔ በማሳለፍ ከክልሉ ወጥቷል፡፡ ነገር ግን ልዩነትን በግጭት ብቻ ከመፍታት ውጭ ሌላ የአማራጭ መንገድ ያለ የማይመስለው የሽብር ኃይሉ ትህነግ በከፈተው ዳግም ወረራ በአማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ ንጹሐን የጦርነቱ ሰለባ ሲሆኑ ሃብት እና ንብረት ተዘርፏል፤ ወድሟል፡፡ በሽብር ቡድኑ ወረራ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት የተዳረጉት ወገኖች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በሁለቱ ክልሎች ላይ የተፈጠረው ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና መንፈሳዊ ስብራት ጠሊቅ ነው፡፡
አሁን ኢትየጵያውያን አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኃይል በመረጠው መንገድ ወደ ሲዖል ከመሸኘት የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ሰባኪ እንኳን አያስፈልጋቸውም፡፡ በዚህ ወቅት እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በህልውና ዘመቻው እስከ ቀራኒዮ ለመጓዝ የወሰነው ማንንም ለማዳን ሳይሆን ራሱን ለመታደግ እንደሆነ አውቆታል፡፡ በሕዝባዊ ማዕበል ለዘረፋ እና ለወረራ የመጣን ኃይል በሕዝባዊ ማዕበል መመከት ፍትሐዊ ጦርነት ነው፡፡
በሕግ ማስከበርም ሆነ በህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያውያን ተገደው ወደ ጦርነት እንደገቡ እየታወቀ በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግሥት የማንበር ፅኑ ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት በሉዓላዊነታችን የሴራ እጆቻቸውን ሲያስረዝሙ፣ በድህነታችን ሊሳለቁ እና በለጋስነታቸው ሲመጻደቁ አይተናል፡፡ ከሕግ ማስከበር እስከ ሕልውና ዘመቻው ኢትዮጵያ ንጹሐን እንዳይጎዱ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይቋረጥ፣ ባለማወቅ የገቡ ልቦና እንዲገዙ እና የከፋ ውድመት እንዳይፈጠር በተደጋጋሚ የተወሰዱ እርምጃዎች ዋጋ ቢስ ሆነው ሀገር ስትወነጀል አይተናል፡፡ በተቃራኒው የእነዚህ ሁሉ ግጭቶች ጠማቂ የሆነው የሽብር ኃይሉ ቢቻል የአሸናፊነት እድል እንዲያገኝ የተጓዙትን ርቀት ስናይ እውነት እና ፍትሕ እንደተጓደለ ይገባናል፡፡
“እርግጥ ነው በጦርነት ውስጥ ቀድሞ የሚሞተው እውነት ነው፤” እውነት በዚህ ጦርነት ውስጥ ደግሞ እና ደጋግሞ ሲሞት አስተውለናል፡፡ የኢትዮጵያን ምድሯ እና ተፈጥሮ ሃብቷን እንጂ ሰለዜጎቿ ክብር እና ፍቅር የሌላቸው አንዳንድ ምዕራባዊያን እና ቅጥረኞቻቸው ደጋግመው የህልውና ዘመቻውን ዓላማ ሲያጣጥሉ አስተውለናል፡፡ ቢቻል በተላላኪዎቻቸው የበላይነት እንዲቋጭ ባይቻል በተራዘመ ሂደት ኢትዮጵያ ከማትወጣበት ቅርቃር እንድትገባና እንድትንበረከክላቸው እያደረጉ ያሉት ጥረት ሁሉ ገሃድ ወጥቷል፡፡
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን አንድ ምርጫ ብቻ ነው ያላቸው፡፡ የህልውና ዘመቻውን ለዘመናት ታሪካቸው በሚመጥን መልኩ በድል ማጠናቀቅ፤ ለዚህ ደግሞ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ከምድረ ገጽ መጥፋት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ “ሆ” ብለው በተነሱ ጀግኖች ልጆቿ ታሸንፋለች፡፡ እውነት ትመነምን ይሆናል እንጂ አትበጠስምና የኢትዮጵያ እውነት እና አሸናፊነት በቅርብ ይመጣል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ