“ጠላትን ደምስሶ ጀብድ ለመስራት የዘመተ ጀግና ህያው ነው” የፋኖው መሪ አጋየ አድማስ

1480
ደባርቅ፡ ሕዳር 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኹሉም ነገር ለበጎ ነውና! አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በሥልጣን ዘመኑ በመዋቅሩና ከመዋቅሩ ውጪ የፈጸመው አረመኔያዊ ተግባራት ሺህ አርበኞች እንዲፈጠሩ አድርጓል። የቡድኑን ሰይጣናዊ ተልዕኮ የተረዱ በርካታ የአማራ የቁርጥ ቀን አርበኞች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ አይተው በችልተኝነት ለማለፍ አዕምሯቸው ሊፈቅድላቸው አልቻለም።
ቀደም ብሎም አሻፈረኝ! አልገዛም ያሉት ጀግኖች በሞቀ ቤታቸው ሳይኾን ዱሩን ቤታቸው በማድረግ አሸባሪውን ኀይል እንቅልፍ አሳጥተውት ነበር። አርበኞቹ በአልሞ ተኳሽነታቸው ስለሚታወቁ የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ቅጥረኞች፣ ጀግኖቹን ለማጥቃት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።
የጀግንነት ታሪካቸው ተነግሮ ከማያልቀው ፋኖዎች ውስጥ አንዱ፣ ገናናውና ስሙ ከሩቅ የሚያስተጋባው፣ የፋኖ መሪው አጋየ አድማስ ነው። የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን በተከዜ ግንባር በመገኘት ከዚኽ የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ፋኖ አጋየ አድማስ ሺዎች አስፈሪ ጀግኖች ከተፈለፈሉበት ምድር ነው ተወልዶ ያደገው። ፋኖ አጋየ ሕዝብን ሲነኩበት እንጂ ለወዳጁ ትሁት፣ ልቡ የሚራራና ሰው አክባሪ ነው። ፋኖ አጋየ ልክ እንደ ሌሎች ጓዶቹ ወያኔ በአማራ ላይ የሚፈጽመውን ግፍ ላለማየትና መራራ ትግል ለማካሄድ በ1997 ዓ.ም ጀምሮ ሥርዓቱ እስኪገረሰስ ድረስ ዱሩን ቤቱ ማድረግ ጀመረ። ከትግል ጓዶቹ ጋር በመኾን የአማራ ምድር በኾነው በአርማጭሆና በጠገዴ ጫካ የጠላትን አከርካሪ መቁረጥ እንደጀመሩ ቆፍጣናው ፋኖ ተናግሯል።
በትግል ዘመኑ ጠላትን በመደብደብ ልምድን ያካበተው የፋኖው መሪ፣ በቅርቡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ወረራ በፈጸመበት በደቡብና በሰሜን ጎንደር ዞኖች እንዲኹም በተለያየ አካባቢ ከትግል ጓዶቹ ጋር በመዘዋወር ጠላትን እንደ ቅጠል ማርገፋቸውን ገልጿል። “ጠላት የፋኖን የብረት በትር ጠንቅቆ ያውቀዋል” ያለው ፋኖ አጋየ፣ ባካሄዱት አውደ ውጊያ ኹሉ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቁሟል።
ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከአማራ ልዩ ኀይል ጋር እጅና ጓንት ኾነው በግንባር ቀደምትነት የጠላትን ምሽግ ሲሰብሩ እንደነበረ ተናግሯል። “ተቆጥሮ የተሰጠንን ሥራ ቆጥረን ነው የምናስረክበው” ነው ያለው። የሀገር መከላከያ ሠራዊት “ፋኖ ከጎኔ ካለ እተማመንበታለሁ” ብሎ እንደሚያደንቅ የተናገረው ፋኖ አጋየ፣ ፋኖ በኹሉም ተግባር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በጋራ እየሠራ መኾኑን አስረድቷል።
ፋኖ ከሌሎች የትግል አጋሮቹ ጋር በመኾን ወረራ የፈጸመውን የጠላት ቡድን በገባበት እንዲቀር የማድረግ ትግል እንዳካሄደና እንደሚያካሂድ አስገንዝቧል። ፋኖ ጠላትን ለመደምሰስ ጠንካራ ቁመና እንዳለው ቆራጡ ፋኖ አጋየ አረጋግጧል። ጠላት እስኪወገድ ድረስ ፋኖ ከጫካው እንደማይወጣ አስገንዝቧል።
አርበኛው አጋየ የአማራ ሕዝብ ጠላትን ለማጥፋት እንደ ማእበል መንቀሳቀሱን አድንቋል። በመኾኑም ሕዝቡ ወደ ትግል ሲገባ በቆራጥነት መንፈስ የሞራልና የዓላማ ስንቅ ሰንቆ መዝመት እንዳለበት ምክሩን ለግሷል።
ዘማቹ ኀይል ጠላትን የመደምሰስ ወኔ ሊሰንቅ ይገባል ነው ያለው። “በከተማ በየ መጠጥ ቤቱ በመዞር የሚጨፍር፣ በተለያየ ደባል ሱስ የተጠመደ ወጣት የወገን ሳይኾን የጠላት ደጋፊ ነው። ወጣቱ ምቾትን ወደ ጎን በመተው ለሕልውናው መታገል አለበት” ያለው ፋኖ አጋየ ጠላት እድሜና ፆታ ሳይለይ ወራሪ ኀይል በማዝመቱ ጠንካራ የኾነ የሕዝብ ምላሽ ያስፈልገዋል ብሏል። “ጠላትን ደምስሶ ጀብድ ለመሥራት የዘመተ ጀግና ህያው ነው፣ የአማራ ሕዝብም ተጭኖበት የነበረውን የጭቆና ግፍ ዳግም እንዲመለስ መፍቀድ የለበትም” ብሏል።
ፋኖ አጋየ እንዳለው ጠላት እስኪጠፋ ድረስ ሕዝቡ ከትግል ሜዳ ሳይለይ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። “የሕዝብ ሞራል የሚያገኝ የወገን ኀይል ሕይወቱን ለመስጠት አይሳሳም” ነው ያለው።
አርበኛው ፋኖ አጋየ፣ ፋኖ ምንም አይነት የአቅርቦት ችግር ሳያጋጥመው እንዲታገል ላስቻለው ሕዝብም ምስጋናውን አቅርቧል። ሕዝቡ ከእለት ጉርሱ በመቀነስ ያደረገልን ድጋፍ በትግል ታሪካችን ተመዝግቦ ይቀመጣል ብሏል። ትግሉ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስቧል።
ዘመቻውን እያስተባበሩ ከሚገኙት ውስጥ ሱሌይማን ዓለማየሁ ፋኖ አጋየ ለአማራ ሕዝብ ተምሳሌት የሚኾን ቆራጥ፣ ታግሎ የሚያታግል ነው ብለዋል። ፋኖ አጋየ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ሠርቶ የሚያሳይ ቆራጥ ታጋይ በመኾኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ እንደሚያደንቁት ነው የተናገሩት። “አጋየ ትሁትና ጀግና፣ በጽናት የሚታገል፣ ለገንዘብ የማይሠራ አርአያ መኾን የሚገባው ታጋይ ነው” ነው ያሉት። ባለፉት ጊዜያት በነበረው ትግል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ የፋኖ አጋየና የፋኖ ሰፈር ጓዶች በግራና ቀኝ በመኾን ውጤታማ ድልን ማስመዝገብ እንደቻሉ ጠቁመዋል።
ፋኖ የአማራ ሕዝብ የጀርባ አጥንት ነው ያሉት ሱሌይማን ሕዝቡ ትክክለኛ ለሕዝብ ነፃነት የሚታገሉትን ፋኖዎች በመለየት መደገፍና አክብሮት መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
“በየከተማው ማኅበራዊ ድረ ገጽን በመጠቀም በፋኖ ስም ገንዘብ ለማካበት የሚጥሩትን ኅብረተሰቡ ሊያወግዛቸውና ሊያገልላቸው ይገባል” ብለዋል። ፋኖ ለሕዝብ ነፃነት በራሱ ኪስ የሚታገል እንጂ ከሕዝብ ጥቅም የሚፈልግ እንዳልኾነ ጠቁመዋል። ከሕዝቡ የሚገኘው ድጋፍ ለትግል የሚውል ቁሳቁስ መግዣ እንጂ ለግለሰብ አይውልም ያሉት ፋኖ ሱሌይማን የሚደግፉ አካላትም ይኽን ጠንቅቀው ሊረዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከተከዜ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመን ይህንን ጊዜያዊ ማዕበል ከፍለን በአንድነት እንድናቋርጠው እጠይቃለሁ❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article❝…የተጋረጠብንን የህልውና ስጋት አንድ ሆነን ማሸነፍ እንችላለን❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)