
ደባርቅ፡ ሕዳር 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይልን ለመደምሰስ ዱር ቤቴ ብለው ጠላትን እየተፋለሙ የሚገኙ ፋኖዎችን አነጋግሯል። በርካታ ጀግና አርበኞች የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይልን ሀገር ማፍረስ ተልዕኮ ከመሰረቱ በመረዳት ሕይወታቸውን በሙሉ በጫካ በማሳለፍ ሲታገሉ ቆይተዋል። በትግላቸውም ጠላት እንዲወድቅ የበኩላቸውን ታላቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል። በሺዎች ከሚቆጠሩ ታጋይ አርበኞች ውስጥ ለዛሬ አንድ ታዋቂ፣ ስመጥርና አኹንም ከጓዶቹ ጋር በመኾን በማይጠብሪ ግንባር ጠላትን እየቀጣ ከሚገኘው የፋኖ ብርጌድ አዛዥ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ሻለቃ ሰፈር መለሰ ተወልዶ ያደገው በአዳርቃይ ወረዳ በዛሪማ ከተማ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ ለፍትሕና ለእኩልነት ሲታገል ያደገው ሻለቃ ሰፈር በ1981 ዓ.ም የአሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይል ሴራ ቀድሞ በመረዳት አሻፈረኝ ብሎ ወደ ጫካ ገባ። በወቅቱ ቡድኑ ዛሪማንና አካባቢዋን በተቆጣጠረበት ወቅት ቀድሞ የጠላትን ሴራ የተረዳው ሻለቃ ወገኑንና ሀገሩን ለማዳን የጠላትን ሴራ በማፍረስ የትግል ሕይወቱን ጀመረ።
“ዛሬ መላው ኢትዮጵያውያን የተረዱትን የአሸባሪ ኀይሉን ሴራ እኔና ጓዶቼ ቀድመን ነበር የተገነዘብነው” ያለው ቆፍጣናው ፋኖ ኹሉም ኢትዮጵያዊ የጠላትን ሴራ ቀድሞ ቢረዳ ኖሮ ይኽን ኹሉ ጥፋት ለማድረስ እድል አያገኝም ነበር ብሏል። በሽብር ቡድኑ የሥልጣን ዘመን በተሽከርካሪ ተጭኖ ወደ ትግራይ እየተወሰደ ሳለ አርበኛው በጀግንነት ወኔ ጠላቶቹን እንደቅጠል ማርገፍ እንደቻለ አስታውሷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከበርካታ ጓዶቹ ጋር በመኾን ዱሩን ቤቱ አድርጎ ለሀገሩ ነፃነት ሲታገል እንደኖረ ተናግሯል። “እኔና ወያኔ ከጦርነት ውጪ አንተዋወቅም” ብሏል።
አርበኛው ፋኖ ሻለቃ ሰፈር በትግል ዘመኑ ሰባት ጊዜ ጠላት በጥይት ቢያቆስለውም ለጠላት ሳይንበረከክ የሚፈለገውን ለውጥ ካመጡት ጀግኖች ውስጥ አንዱ ለመኾን በቅቷል። አሸባሪው ኀይል ከምስረታው ጀምሮ ዜጎችን ሲጨፈጭፍ እንደቆየ ያወሳው ቆፍጣናው ፋኖ አኹን ላይ መላው ሕዝብ የሸብር ኀይሉን ሴራ በመረዳት ለዘመቻው መነሳቱ የሚያስደስትና የሚበረታታ እንደኾነ ገልጿል።

“እኛ የአሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይልን ሴራ ቀድመን በመረዳት ትግል ብናካሂድም በርካታ ፋኖዎች በየአካባቢው የሽብር ኀይሉን ታግለዋል። ፋኖ ማለት ከደመወዝና ከጥቅማጥቅም ውጪ ለሀገሩ ነፃነት የሚታገል ጀግና ነው” ብሏል። ሻለቃ ሰፈር የፋኖ ደመወዝ የሕዝብ ነፃነትና የሕዝብ ፍቅር እንደኾነ ነው የተናገረው።
ፋኖ ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ተጋድሎ ጠላትን እየቀጠቀጠ እንደኾነ ጠቁሟል። “አኹን የሀገረ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ የሽብር ኀይሉን የሀገር ማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ በአንድነት እየታገሉት ነው” ያለው ሻለቃ የፋኖ አደረጃጀትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ መኾኑን አረጋግጧል። አኹን ላይ ፋኖ በየአውደ ግንባሩ ተልዕኮን በመቀበል የሽብር ኀይሉ የሚረግጠው መሬት እሳት እንዲኾንበት አድርጓል፤ እያደረገም ነው ይላል።

“አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል የአማራን ሕዝብ ሕይወቱን፣ ሀብቱን፣ ሀገሩንና ቤተ እምነቱን ኹሉ ስላሳጡት ሆ! ብሎ መነሳቱ ተገቢ ነው” ብሏል። በየከተማው ፋኖ ነን ብለው ጥይት የሚተኩሱ፣ ሕዝብን የሚያስፈራሩ፣ የሚያሸብሩ፣ ሕዝብን የሚበድሉ ጸረ ሕዝብ እና ዘራፊዎች እንጂ ፋኖ እንዳልኾኑ ሕዝቡ መረዳት ይኖርበታል ነው ያለው። ፋኖ ነኝ የሚል ኹሉ በአንድነት የቆመ፣ በሕግ የሚመራ፣ አምርሮ ለሕዝብ የሚታገል መኾን እንዳለበት አሳስቧል። ኅብረተሰቡም ድጋፍ ሲያደርግ ትክክለኛ ለሀገር የሚታገሉ ፋኖዎችን በመለየት መኾን አለበት ነው ያለው። “ኅብረተሰቡ የማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀሚያ በመኾን በረሃን ላልቀመሰ ፋኖ ድጋፍ ማድረግ የለበትም” ብሏል።

በታሪክም ቢኾን ባንዳነት እና ክህደትን የሚጠላው አማራ አኹንም ባንዳውን አምርሮ መታገል እንዳለበት አስገንዝቧል። “አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል የሚታገለው ሀገርን ለባንዳ ለመሸጥ እንጂ ሀገር ለማስተዳደር አይደለም፤ በታሪክም ቢኾን መገለጫው ባንዳነት ነው” ነው ያለው።
የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበት አደጋ የመኖርና ያለመኖር ስለኾነ አማራ ማንኛውንም ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ መታገል እንዳለበት አርበኛው አሳስቧል። “ጠላት ሆ! ብሎ አማራን ለማጥፋትና ሀገርን ለማፍረስ እንደተነሳው ኹሉ መላው ኢትዮጵያውያን በተለይ አማራ ሆ! ብሎ ሀገር የማዳን ትግል ሊያደርግ ይገባል” ብሏል። ከበቂ ምክንያት ውጪ ጥይትን የሚያባክን ሰው ትክክል እንዳልኾነ የጠቆመው አርበኛው አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት እንጂ በየሜዳው መተኮስ እንደሌለበት አሳስቧል። “የትግል ጓዶቻችን ቢሰው ደማቸውን የምንመልሰው ጠላትን በማጥቃት እንጂ ጥይትን በማጮህ አይደለም ነው” ያለው።
አርበኛው ፋኖ ሻለቃ ሰፈር ከትግል ጓዶቹና ከወገን ኀይል ጋር በመሰለፍ የጥፋት ኃይሉ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከዛሪማ
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ